Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

General

የፊደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የባለስልጣኑን የዝግጅት ምዕራፍ የሪፎርም ስራዎችን ገመገመ፡፡

(ግንቦት19/2017ዓ/ም) በመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ስርዓት ውስጥ በየዘርፉ የሚስተዋሉ የአሰራር ማነቆዎችን ነቅሶ በማውጣት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚያስችለው ፖሊሲ ከመጽደቁ በተጫማሪ ከፖሊሲው የሚቀዳ የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር የሪፎርም ስራ ተቀርጾ ወደ ትግበራ መገባቱ ይታወቃል፡፡

ሪፎርሙን በውጤታማነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የሪፎርም ትግባራ የሚመራበት አግባብ፣የትግበራ ምዕራፎችን እና የሚከናወኑ ተግባራትን በግልጽ የሚያመላክት እና አቅጣጫ የሚጠቁም ፍኖተ ካርታ ጭምር ተዘጋጅቶለት ለተግባራዊነቱ ወደ ተቋማት ወርዷል፡፡

ይህንን ሃገራዊ ተልዕኮ ለማስፈጸም ከተመረጡት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የዝግጀት ምዕራፉን በተሻለ አፈጻጸም አጠናቋል፡፡ ይህን ተከትሎ በዛሬዉ ዕለት ትግበራዉን ለመደገፍ እና ለመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው የፌደራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ልዑኩን ለዚሁ የሪፎርም ስራዎች የዝግጀት መርሃ-ግብር ግምገማ በስፍራው አሰማርቷል፡፡

ልዑኩን ተቀብለው ያነጋገሩትና የተጠናቀቀዉን የዝግጅት ምዕራፍ የሪፎርም ስራዎች እንዲገመግም ተግባራቱን አደራጅተው የጠበቁት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ በሪፎርም ስራዎች የተከናወኑ ተግባራትን አንድ በአንድ በሰነድ ማስረጃዎች ጭምር በማስደገፍ በገለጻቸውን አቅርበዋል፡፡

በዝግጅት ምዕራፍ ከተተገበሩት የሪፎርም ስራዎች ውስጥ በዋናነት የተቋሙን ዌብሳይት፣ የe-learning የመማሪያ ስርዓት፣ዘመናዊ የደብዳቤ ልዉዉጥ ስርዓት( Letter management system)በራስ አቅም አልምቶ መተግበሩ፣የነዳጅ አጠቃቀምና የተሸከርካሪ ስምሪት (e-fleet management)፣እየተዘጋጁና እየተተተገበሩ የሚገኙ መመሪያዎች፣አዋጁን አካታች ለማድረግ በምልክት ቋንቋ እና በብሬል ጭምር በማሳተም የተሰሩ ተግባራት፣ ለሴቶች እና ህጻናት እንዲሁም ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተተገበሩ ምቹ የስራ አካባቢን የመፍጠር ትግበራዎች፣ የe-GP ሲስተምን ተጠቃሚ ተቋማት የማስፋት እና የሲስተም ማሻሻያዎችን የማከናዎን ተግባራት፤የሲስተም ትስሰር ከሌሎች ተቋማት ጋር መፈጠሩ፤ተገልጋዩች ባሉበት ሆነው እገዛ የማግኘት፤ቅሬታ የማቅረብ እና ምላሽ የመቀበል አሰራርን ያካተተ የሲስተም ማሻሻያ ትግበራ መዘርጋቱ፣የተገልጋዩች ቻርተር መዘጋጀቱ፣ ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታና ሙያዊ ስልጠናዎችን እንዲሁም ሌሎች ሰፊ የሪፎረም ስራዎች መከናወናቸውን በገለጻቸው አካትተዉ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሠነድ ማረጋገጫ ጭምር በማቅረብ አሳይተዋል፡፡

ልዑኩ በቀረበው ገለጻ ላይ ተመርኩዞ በተግባር ማየት የሚፈልጋቸውን ሁሉም ሰነዶች ቀርበውለት የተመለከተና በተጨባጭ መተግበሩን ጭምር ለማረጋገጥ ተዘዋሮ በመጎብኘት ያረጋገጠ ከመሆኑም ባሻገር በአፈጻጸሙ እጅግ ደስተኞች መሆናቸውን በማስቀደም፤ በተለይም ለሰራተኞች ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር የተሄደበት እርቀት እና አገልግሎት አሰጣጡን ከማዘምን ጋር የተያያዙት ትግበራዎች ልዑኩ ከተሰማራበትና ልዩ ትኩረቱን አድርጎ ከሚገመግመበት አጀንዳዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለዉ ጥሩ አፈጻጸም መሆኑን አበክረዉ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም በልዩነት ሴት ሰራተኞችን ለመደገፍ እና ለማብቃት እየተከናወነ ያለው ቁልፍ ተግባር፣ ሠራተኞች ያለችግር ልጆቻቸው እየተከታተሉ እንዲሰሩ የተዘጋጀው የህጻናት ማቆያ፣ አዋጁን አካታች ለማድረግ የተሄደበት እርቀት (ብሬልን እና የምልክት ቋንቋን መጠቀሙ)፤ድህረ-ገጽ እና የe-learning ፕላትፎርም በራስ አቅም አልምቶ ወደ ተግባር መገባቱ እና አሰራርን በተለይም የግዥን ስርዓቱን ለማዘመን የተፈጸሙ ተግባራት ይበል የሚያሰኝ እና ለሌሎች ተቋማት ጭምር ለማሳያነት ሊውል የሚችል መልካም አፈጻጸም የታየበት ድንቅ ተግባር ነው ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ልዑኩ በተገኘበት ወቅት የገንዘብ ሚኒስቴር ልዑክም እንደ ተጠሪ ለመደገፍና ለመከታተል በስፍራው ተገኝቷል።

በመጨረሻም የተከናወኑ ተግባራትን ተጨባጭነት ለማረጋገጥ የህጻናት ማቆያዉን ጨምሮ ሁሉንም የስራ ክፍሎች ተዟዙረዉ ጎብኝተው የግምገማ መረሃ-ግብሩ ፋጻሜውን አግኝቷል፡፡

ከሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ እና ከፌደራል ዋና ኦዲተር ኃላፊዎች ጋር በነበረው የውይይት መድረክ የተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች፤ሃሣብ እና አስተያየቶች ከተሰጡ ማጠቃለያዎች ጋር

(ግንቦት20/2017ዓ/ም) ከቀረበው ሰፊ ገለጻ በኋላ በሁለቱም ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና አባላት እንዲሁም የፌደራል ዋና ኦዲተር የስራ ኃላፊዎች ግልጽነት የሚሹ ጥያቄዎች እና ሃሳብ አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

ዕድሉን የወሰዱ ተሳታፊዎች የኢጂፒ ሲስተም በሁሉም የፌደራል ተቋማት እና በ93 ቅርንጫፎቻቸው ከመስፋፋቱም ባለፈ ለሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጭምር ለተሞክሮ ማጋሪያነት መዋሉ፣ሪፎርሙን ከአዋጅ ጋር አስተሳስሮ መተግበሩ፣ አዋጅ ቁጥር (1333/2016) ለማስተግበር የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎችን ለማዘጋጀት የተደረገው ጥረት፣ የአዋጁን አካታችነት እና ተደራሽነት ለማሳለጥ በምልክት ቋንቋና በብሬል ጭምር መታተሙ፣ በአመራሮች እና ባለሙያዎች ላይ የነበረው ቁርጠኝነት፣ በመርህ ደረጃ የሚወሩ ህጎችን በተግባር ለማሳየት የተደረገው ጥረት እና መሠል ጉዳዮች በአዎንታዊነት ከተነሱት መካከል ይገኙበታል፡፡

ከሲስተሙ ጋር ተያይዞ ከደህንነት ፖሊሲ፣ነጋዴው ማህበረሰብ ሲስተሙን መጠቀም እንዲችል ግንዛቤ ከማሳደግ ጋር በተያያዘ፣ የተጠቃሚዎች የእርካታ ዳሰሳ ከመተግበሩ ጋር የተያያዙ፣ ከሲስተም ትስሰር እና ቴክኖሎጂውን ከሚያስተዳድር የስራ ክፍል ጋር የተያያዘ እና መሰል ጉዳዩች ግልጽነትት ከሚሹት ጎራ ተነስተዋል፡፡

ከአጠቃላይ የተቋሙ የስራ እንቅስቃሴና አዲሱ አዋጅ ጋር በማስተሳሰር ከተነሱት መካከል ደግሞ አዋጁን ለማስፈጸም የሚዘጋጁ መመሪያዎች መዘግየት፤ የደንብ አለመወጣት፣ የሚያስፈልጉ ማሻሻያዎችን አጥንቶ ከማቅረብ አኳያ እና መሰል ተያያዥ ጉዳዩች ምላሽ ከሚሹት መካከል ይገኙበታል፡፡

በመቀጠልም የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ የመድረኩ ዋና ዓላማ እየሰራን ያለውን ገልጸን የሚሰጡ ሃሳቦችን ወስዶ ለማሻሻል ስለሆነ የተነሱ ሃሳቦችን በግብዓትነት የምንወስድ ሲሆን በቀጣይ ወደ ዕቅድ በመቀየር ተግባራዊ እናደርጋቸዋለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም የተሰጡ አዎንታዊ አስተያየቶች በሙሉ ውጤታቸው የተመዘገበው በአመራሩ ቁርጠኝነት ብቻ ሳይሆን ሲስተም ካለማው አካል ጀምሮ ባለሙያዎች በኃላፊነት ስሜት ያከናወኗቸው ተግባራት የጋራ ድምር ዉጤት በመሆኑ አድናቆቱ ለሁሉም ይድረስ ሲሉ ተሰምተዋል፡፡

አያይዘዉም ለተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ጥቅል ተቋማዊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በተለይም ኢጂፒ ሲሰተም ሙሉ በሙሉ ሊያስገኝ የሚገባው ጥቅም እንዲስያገኝ ከማድረግ አኳያ፣ተቋማት የግዥ ስራዎችን ከሲስተሙ ጋር አስተሳስረው እንዴት እየተገበሩ እንዳለ የመደገፍ ሂደት ላይ፣ከሲስተሙ ደህንነት ፣ለንግዱ ማሀበረሰብ ሊሰጥ ከሚገባዉ ግንዘቤ የማሰጨበጥ ተግባር፣አዋጁ መመሪያ እንዲወጣላቸው በሚፈቅድላቸው ጉዳዩች ላይ መመሪያዎችን በማውጣት ረገድ፣ የባለስልጣኑን ድጋፍ በሚሹ በሁሉም ተቋማዊ ጉዳዮች፣የፌደራል ቅርንጫፍ መ/ቤቶችንና ክልሎችን ወደ ሲስተሙ በማስገባት ረገድ እና መሰል ተግባራት ላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በህዝብ ተወካዩች ም/ቤት የፕላንና ልማት እና ፋይናስ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ በማጠቃለያ ንግግራቸው ምክር ቤቱ አዋጁን ከማዘጋጀት እና ከማጽደቅ ባሻገር የመከታተል እና መተግበሩን የማረጋገጥ ድርሻ ያለው መሆኑን አስታውሰው ጸድቆ ወደ ተግባር በተለወጠው አዋጅ ደስተኞችና እንደ ሃገርም ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል፡፡

አክለውም ከአዋጁ መጽደቅ በኋላ ትግበራውን የማወቅ ፍላጎት እንደነበራቸዉ ገልጸዉ በዚህ የውይይት መድረክ ያለበት የትግበራ ሂደት ይበልጥ ግልጽ የሆነላቸዉ መሆኑን በማሰቀደም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል በሚሉት ሁሉም ጉዳዩች የግዥዉ ዘርፍ የሃገሪቱን ከፍተኛ በጀት የሚይዝ እንደመሆኑ መጠን ትልቁን ሃላፊነትና የማስፈጸም ድርሻ የተሰጠዉ ባለስልጣኑ ዘመናዊ አሰራርን በሃገራችን ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ ዓለምአቀፍ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ ሊተጋ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ለተሻለ ለዉጥና ተጠቃሚነት በሚያስፈልጉ ማሻሻያዎች ዙሪያ ጥናት በማድረግ ቢመጣ በም/ቤቱ በኩል ማሻሻል የሚቻልበት አግባብ መኖሩን በመጠቆም የዉይይት መርሃ- ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

በመንግስት የልማት ድርጅቶች ደረጃ የመጀመሪያው ስልጠና መስጠት ተጀመረ።

(ሰኔ 03/2017 ዓ.ም) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን አዘምኖ በ2022 በአፍሪካ ግንባር ቀደም የመንግስት ግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም የመሆን ራዕይን ሰንቆ በትጋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይም ስራዎችን በማዘመን፣ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስርዓትን ከማላመድ ተነስቶ የተቋማት ባህል እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፤ ተጨባጭ ለውጦችንም አስመዝግቧል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት 169 የፌዴራል ተቋማት እና 93 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ግዣቸውን በዚህ ስርዓት እንዲፈጽሙ ያደረገ ሲሆን ከተማ መስተዳደሮችና ክልሎችም ስርዓቱን እንዲተገበሩት ለማስቻል ስልጠና እየሰጠና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ይህ እንደተጠበቀ በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን የስርሻቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ተቋማቱን ያሳተፈ አዲስ መመሪያ ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል።

በፌዴራል መንግስት ስር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን አዲሱ መመሪያ የልማት ድርጅቶች የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ ስርዓትን እንዲተገብሩ የሚያስችል በመሆኑ በልማት ድርጅቶች ረገድ የመጀመሪያው ስልጠና ለኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩብ እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስርዓት ምንነት፣ አተገባበር እና ፋይዳ እንዲሁም የመንግስት ግዥና ንብረት አዲሱ አዋጅ ምንነትና ሌሎች መመሪያዎች ላይ የሚያተኩር ነው።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩብ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ሲሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ለሚያደርጉላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግነው ስልጠናው በግዥ ሂደት የሚስጠዋሉ ችግሮችን የምንቀርፍበትና በጊዜ፣ በገንዝብ፣ በጥራትና በተወዳዳሪነት ውጤታማ የምንሆንበት በመሆኑ ሁሉም በንቃት መከታተል እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

ስልጠናው ዛሬ በኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ ስርዓት ምንነት፣ አተገባበር እና ፋይዳ ላይ ሲያተኩር ስልጠናውን የሰጡት የመንግስት ግዥና ንብረት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በስልጠናቸው የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) አፈጻጸማና ሂደትን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዓላማን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዋና ዋና ተጠቃሚዎችን፣ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ አሁን ያለበትን ደረጃ፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ያስገኘውን ውጤትና የነበሩ ተግዳሮቶችን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በስልጠናው ውድድርና እኩል እድል መስጠት፣ ገንዘብ የሚያስገኘውን ዋጋ ማስገኘቱ፣ የመንግስትን ህግ ማክበር፣ ወጪን መቀነስ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዓላማዎች ተብለው የተጠቀሱ ሲሆን ለውጥን ለመቀበል መዘግየት የመሳሰሉት በተግዳሮትነት የቀረቡ ጉዳዮች ናቸው።

በሌላ በኩል መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ አዋጅን ማሻሻል፣ የጥሪ ማዕከል ማደራጀት፣ የሲስተም ልማት፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሲስተም ትስስር መፍጠር ስርዓቱን ለመገንባት ከተከናወኑ ተግባራት ጥቂቶች መሆናቸውን ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው አካትተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ያስገኘውን ጥቅም በሚመለከት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያካሄደ መሆኑን አንስተው በጥናቱም ስራ ያቀላጠፈ መሆኑን፣ ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን፣ የህግ ተፈጻሚነት እንዲረጋገጥ ያስቻለ መሆኑን፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን፣ ውጪን የሚቀንስ መሆኑን፣ የሰነድ ማጭበርበርን ማስቀረቱን በጥናቱ መረጋገጡን አብራርተዋል። 

በመጨረሻም ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ስልጠናው ነገም የሚቀጥል ይሆናል።

በቁልፍ የግዥ አፈጻጸም፣በክልል የወረዳ ግዥ ኦዲትና በካልም ኦዲት ዙሪያ ዉይይት ተካሄደ፡፡

(ግንቦት10/2017ዓ/ም) ባለስልጣኑ ላለፉት ሁለት ቀናት በደብረዘይት ከተማ ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት ከክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ዉይይት ለማድረግ ከያዛቸዉ አጀንዳዎች ዉስጥ አንዱና የመጨረሻዉ የሆነዉ ቁልፍ የግዥ አፈጻጸም አመላካቾች (KPI) ዙሪያ የ2016ዓ/ም አፈጻጸምን የሚዳስስና የተሻለ የተገበሩ ክልሎች ተሞክሯቸዉን የሚያጋሩበት ብሎም የወረዳ ግዥ ኦዲትና የካልም (KALM) ወረዳዎች ኦዲት የአፈጻጸም ሪፖርት የሚቀርብበት መርሃ-ግብር ነዉ፡፡

አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጥቅል ሪፖርቱን ያቀረቡ ሲሆን የክልሎችን አፈጻጸም በንጽጽር በማመላከት አፈጻጸማቸዉ የተሻለዉን በተሞክሮነት እንዲወስዱና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸዉ ደግሞ መሻሻል እንዲችሉ ዕድል በሚሰጥ መልኩ አቅርበዋል፡፡

አስተባባሪዉ ከግዥ ኦዲት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ባደረሱበት ወቅት የኦዲት ዋነኛ ዓላማ የተከናወኑ ተግባራት ትክክለኛዉንና የተናበበዉን ሂደት ተከትለዉ መተግበራቸዉን ለማረጋገጥና ስህተት በተፈጠረ ጊዜም ተጨማሪ የማስተካከያ ዕድል ለመስጠት የሚያሥችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክልዉም ከየወረዳዎቹ የሚላኩ የኦዲት ሪፖርቶች የተገኘዉን ዉጤት ብቻ ሳይሆን አስቻይ ሁኔታዎችን፣ለሚያጋጥሟቸዉ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችንና ግብረ-መልሶችን ሊያካትቱ እንደሚገባና የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበና በሚመጥን መንገድ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየታቸዉን በሰጡበት ወቅት ለሰነድ ዝግጅቱና ለአቀራረቡ ብሎም ባለስልጣኑ ለትግበራዉ ላሳየዉ ቁርጠኝነት ያላቸዉን አድናቆት በማስቀደም ከKPI ሲስተም ምዝገባ፣ከቢሮ ኃላፊዎች ትኩረት ማነስና ከ ማጽደቅ( Approval) ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ምላሽ ከሚሹት ጎራ አንስተዋል፡፡

ለተነሱ ጉዳዮች የፕሮጀክት አስተባባሪዉን ጨምሮ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ ማጠቃለያ የሰጡ ሲሆን ዘርፉ ከልማት እንቅስቃሴዎች ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለዉ ስለሆነ በተለይም ለቁልፍ የግዥ አመላካቾች በቂ ትኩረት በመስጠት ሊተገበር እንደሚገባ እና የ2017ዓ/ም ሪፖርት ወቅቱን ጠብቆ እንዲላክ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣኑ በማንኛዉም የትግበራ ሂደት የተለመደ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ መርሃ-ግብሩ ተጠናቅቋል፡፡