Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

General

በመንግስት የልማት ድርጅቶች ደረጃ የመጀመሪያው ስልጠና መስጠት ተጀመረ።

(ሰኔ 03/2017 ዓ.ም) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን አዘምኖ በ2022 በአፍሪካ ግንባር ቀደም የመንግስት ግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም የመሆን ራዕይን ሰንቆ በትጋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይም ስራዎችን በማዘመን፣ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስርዓትን ከማላመድ ተነስቶ የተቋማት ባህል እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፤ ተጨባጭ ለውጦችንም አስመዝግቧል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት 169 የፌዴራል ተቋማት እና 93 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ግዣቸውን በዚህ ስርዓት እንዲፈጽሙ ያደረገ ሲሆን ከተማ መስተዳደሮችና ክልሎችም ስርዓቱን እንዲተገበሩት ለማስቻል ስልጠና እየሰጠና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ይህ እንደተጠበቀ በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን የስርሻቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ተቋማቱን ያሳተፈ አዲስ መመሪያ ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል።

በፌዴራል መንግስት ስር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን አዲሱ መመሪያ የልማት ድርጅቶች የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ ስርዓትን እንዲተገብሩ የሚያስችል በመሆኑ በልማት ድርጅቶች ረገድ የመጀመሪያው ስልጠና ለኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩብ እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስርዓት ምንነት፣ አተገባበር እና ፋይዳ እንዲሁም የመንግስት ግዥና ንብረት አዲሱ አዋጅ ምንነትና ሌሎች መመሪያዎች ላይ የሚያተኩር ነው።

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩብ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ሲሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ለሚያደርጉላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግነው ስልጠናው በግዥ ሂደት የሚስጠዋሉ ችግሮችን የምንቀርፍበትና በጊዜ፣ በገንዝብ፣ በጥራትና በተወዳዳሪነት ውጤታማ የምንሆንበት በመሆኑ ሁሉም በንቃት መከታተል እንደሚኖርበት አሳስበዋል።

ስልጠናው ዛሬ በኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ ስርዓት ምንነት፣ አተገባበር እና ፋይዳ ላይ ሲያተኩር ስልጠናውን የሰጡት የመንግስት ግዥና ንብረት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በስልጠናቸው የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) አፈጻጸማና ሂደትን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዓላማን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዋና ዋና ተጠቃሚዎችን፣ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ አሁን ያለበትን ደረጃ፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ያስገኘውን ውጤትና የነበሩ ተግዳሮቶችን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በስልጠናው ውድድርና እኩል እድል መስጠት፣ ገንዘብ የሚያስገኘውን ዋጋ ማስገኘቱ፣ የመንግስትን ህግ ማክበር፣ ወጪን መቀነስ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዓላማዎች ተብለው የተጠቀሱ ሲሆን ለውጥን ለመቀበል መዘግየት የመሳሰሉት በተግዳሮትነት የቀረቡ ጉዳዮች ናቸው።

በሌላ በኩል መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ አዋጅን ማሻሻል፣ የጥሪ ማዕከል ማደራጀት፣ የሲስተም ልማት፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሲስተም ትስስር መፍጠር ስርዓቱን ለመገንባት ከተከናወኑ ተግባራት ጥቂቶች መሆናቸውን ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው አካትተዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ያስገኘውን ጥቅም በሚመለከት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያካሄደ መሆኑን አንስተው በጥናቱም ስራ ያቀላጠፈ መሆኑን፣ ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን፣ የህግ ተፈጻሚነት እንዲረጋገጥ ያስቻለ መሆኑን፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን፣ ውጪን የሚቀንስ መሆኑን፣ የሰነድ ማጭበርበርን ማስቀረቱን በጥናቱ መረጋገጡን አብራርተዋል። 

በመጨረሻም ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ስልጠናው ነገም የሚቀጥል ይሆናል።

በቁልፍ የግዥ አፈጻጸም፣በክልል የወረዳ ግዥ ኦዲትና በካልም ኦዲት ዙሪያ ዉይይት ተካሄደ፡፡

(ግንቦት10/2017ዓ/ም) ባለስልጣኑ ላለፉት ሁለት ቀናት በደብረዘይት ከተማ ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት ከክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ዉይይት ለማድረግ ከያዛቸዉ አጀንዳዎች ዉስጥ አንዱና የመጨረሻዉ የሆነዉ ቁልፍ የግዥ አፈጻጸም አመላካቾች (KPI) ዙሪያ የ2016ዓ/ም አፈጻጸምን የሚዳስስና የተሻለ የተገበሩ ክልሎች ተሞክሯቸዉን የሚያጋሩበት ብሎም የወረዳ ግዥ ኦዲትና የካልም (KALM) ወረዳዎች ኦዲት የአፈጻጸም ሪፖርት የሚቀርብበት መርሃ-ግብር ነዉ፡፡

አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጥቅል ሪፖርቱን ያቀረቡ ሲሆን የክልሎችን አፈጻጸም በንጽጽር በማመላከት አፈጻጸማቸዉ የተሻለዉን በተሞክሮነት እንዲወስዱና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸዉ ደግሞ መሻሻል እንዲችሉ ዕድል በሚሰጥ መልኩ አቅርበዋል፡፡

አስተባባሪዉ ከግዥ ኦዲት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ባደረሱበት ወቅት የኦዲት ዋነኛ ዓላማ የተከናወኑ ተግባራት ትክክለኛዉንና የተናበበዉን ሂደት ተከትለዉ መተግበራቸዉን ለማረጋገጥና ስህተት በተፈጠረ ጊዜም ተጨማሪ የማስተካከያ ዕድል ለመስጠት የሚያሥችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክልዉም ከየወረዳዎቹ የሚላኩ የኦዲት ሪፖርቶች የተገኘዉን ዉጤት ብቻ ሳይሆን አስቻይ ሁኔታዎችን፣ለሚያጋጥሟቸዉ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችንና ግብረ-መልሶችን ሊያካትቱ እንደሚገባና የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበና በሚመጥን መንገድ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየታቸዉን በሰጡበት ወቅት ለሰነድ ዝግጅቱና ለአቀራረቡ ብሎም ባለስልጣኑ ለትግበራዉ ላሳየዉ ቁርጠኝነት ያላቸዉን አድናቆት በማስቀደም ከKPI ሲስተም ምዝገባ፣ከቢሮ ኃላፊዎች ትኩረት ማነስና ከ ማጽደቅ( Approval) ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ምላሽ ከሚሹት ጎራ አንስተዋል፡፡

ለተነሱ ጉዳዮች የፕሮጀክት አስተባባሪዉን ጨምሮ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ ማጠቃለያ የሰጡ ሲሆን ዘርፉ ከልማት እንቅስቃሴዎች ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለዉ ስለሆነ በተለይም ለቁልፍ የግዥ አመላካቾች በቂ ትኩረት በመስጠት ሊተገበር እንደሚገባ እና የ2017ዓ/ም ሪፖርት ወቅቱን ጠብቆ እንዲላክ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣኑ በማንኛዉም የትግበራ ሂደት የተለመደ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ መርሃ-ግብሩ ተጠናቅቋል፡፡

በፌደራል የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዐዋጅ ቁጥር 1333/2016 በተካተቱ አዳዲስ ይዘቶችና የተሻሻሉ ጉዳዮች ዙሪያ የውይይት መድረክ ተካሄደ።

(ግንቦት 10/2017ዓ/ም) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ቀደም ሲል በአዋጅ ቁጥር 1333/2016 የጸደቀውን አዲሡን አዋጅ ማስፈጸም የሚያስችሉ የግዥና ንብረት አስተዳደር መመሪያወችን እያዘጋጀ የቆየና ቀደም ሲል የራሱን ሠራተኞች ጨምሮ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት እያወያየ ገንቢ አሥተያየቶችን በማሻሻያነት እየጨመረ አዋጁን ለሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በማስገምገም ግብዓት በማሰባሠብ አበልጽጎ የማስፈጸሚያ መመሪያዎችን አዘጋጅቷል።

ስለሆነም የተናበበና የተጣጣመ የግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓት እንዲኖር ሁሉም ክልሎች አዋጁን መሠረት ያደረገ መመሪያ አዘጋጅተው የአካባቢያቸውን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት መሠረታዊ ህጉንና የአሠራር ሥርዓቱን ሳያዛቡ አዘጋጅተው እንዲተገብሩ እንደሚረዳ ታሥቦ መመሪያውን ከሚቀዱበት አዋጅ አኳያ የተካተቱ አዳዲስ ይዘቶችንና የተሻሻሉ ጉዳዮችን ይፋ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለክልልና የከተማ መስተዳድር ቢሮ ኃላፊዎች በደብረ ዘይት ከተማ ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ነው።

በዐዋጁ የተካተቱ አዳዲስ ይዘቶችና የተሻሻሉ ጉዳዮች የመንግስት ግዥ ማሻሻያ አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በሆኑት አቶ መላኩ ተጓዴ የቀረበ ሲሆን በዋናነት አዲሡ አዋጅ ከነባሩ ያለውን ጉልህ ልዩነት በማሳየትና የተደረጉ መሠረታዊ ማሻሻያዎችና የተካተቱ አዳዲስ ይዘቶች ላይ ልዩ ትኩረቱን ያደረገ ማብራሪያ ለተሳታፊዎች አቅርበዋል።

መሪ ሥራ አስፈጻሚው አክለውም ክልሎች ከአዋጁ ጋር የተናበበና የተቀራረበ የማስፈጸሚያ መመሪያቸውን ሲያዘጋጁ ሀገራዊ የግዥና ንብረት አስተዳደር መመሪያ የማስፈጸሚያ ህጎችን ባስጠበቀ መልኩ ስለሚሆን ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥመው መመሪያ አዘጋጅተው ለመፈጸም እንዲችሉ ስለሚረዳ የተሻሻሉ እና እንደ አዲስ የተካተቱ ይዘቶችን ልዩ ትኩረት ሠጥቶ
መረዳቱ አስፈላጊ መሆኑንን ተገንዝበው ሊሻሻል ይገባል በሚሉት ዙሪያም ሀሳብ አስተያየታቸውን ለተጨማሪ ግብዓትነት ሊሠጡ እንደሚገባ በገለጻቸው ወቅት አሳስበዋል።

በመቀጠልም ተሳታፊዎች ባለሥልጣኑ እየተገበረ ያለው መሠረታዊ ተግባሮች በቂ ዝግጅት የተደረገበትና ሀገሪቱን የሚመጥን
መሆኑን በአድናቆት በመግለጽ፤
ከህይወት ዘመን ወጭ ትንተና፣ከግልግል ዳኝነት፣ከቀጥታ ግዥ ፣ ከክዋኔ ኦዲት ጋርስ ተያያዥነነት ያላቸውና ሌሎች መሠል ጉዳዮችን ተጨማሪ ማብራሪያ ከሚሹ ሀሳቦች መካከል አንስተዋል።

በመጨረሻም የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ ለተነሱ ጉዳዮች የማጠቃለያ ምላሽና አስተያየት የሰጡ ሲሆን

በቀጣይ ባለስልጣኑ የተሻለ የግንኙነት መረብ እንዲፈጠር በማድረግ ለክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ስራዎችና ሥልጠናዎች ላይ በማተኮር የአፈጻጸም ልዩነቶችን የማቀራረብ ተግባር ላይ አበክሮ እንደሚሠራ የገለጹ ሲሆን የምትሠሩባቸው ዘርፎች ከልማት እንቅስቃሴዎች ጋር በቀጥታ የተያያዙ መሆናቸውን በመገንዘብ የቀረበውን ገለጻ በዉይይት ማዳበራቸው የተሰጣቸውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚረዳቸው ሙሉ ዕምነታቸውን ገልጸው ለተሻለ ተፈጻሚነት ከዚህም ባለፈ ባለስልጣኑ በየትኛውም ዘዴ የተለመደ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጭምር በመግለጽ ለዐዋጅ ማሻሻያው የተዘጋጀውን መርሃ -ግብር አጠናቅቀዋል።

በe-GP ሲስተም ትግበራ ዙሪያ የተሞክሮ ማጋራት መርሃ-ግብር ተካሄደ፡፡

(ግንቦት18/2017 ዓ/ም) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የe-GP ሲስተምን በሁሉም የፌደራል ተቋማት እና ቅርንጫፎቻቸው እንዲተገበር ማድረጉን ተከትሎ አዋጭነቱን በጥናት ጭምር በማረጋገጥ ወደ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ለማስፋት አቅዶ ግንዛቤ በመፍጠር ለተግባራዊነቱም እየተጋ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ይህን ጥረት ተከትሎ ተግባራዊ ካደረጉት መካከል አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቅቆ በባለስልጣኑ በተሰጠው ስልጠና እና ድጋፍ መነሻነት ተግባራዊ እያደረገ ለሌሎች ጭምር አርዓያ እየሆነም ይገኛል፡፡ ለዚህም በማሳያነት የተጠቀሰው የአዲስ አበባ ፋይናስ ቢሮ ግንባር ቀደም ሆኖ ተመርጧል፡፡

ቢሮው የተገበረበትን መንገድ በተሞክሮነት ለማጋራት በዛሬው ዕለት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የመጣውን ልዑክ ተቀብሎ ልምዱን አካፍሏል፡፡ በሂደቱም ስልጠናና ድጋፍ ሲያደርግ የቆየው የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የስራ ኃላፍዎችና የሲስተም ባለሞያዎች በጋራ በቢሮው ተገኝተዋል፡፡

ልዑኩን ተቀብለው ያነጋገሩት የአዲስ አበባ ፋይናስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን ሲስተሙን ለመተግበር የሄዱበትን ሂደት አንድ በአንድ አብራርተው በሂደቱ ውስጥ ባለስልጣኑ የነበረው ሚና ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ቀደም ሲል ቢሮው ተግባራዊ ሲያደርገው የነበረውን የማንዋል የግዥ ስርዓት ለማዘመን የኤሌክትሮኒክ የግዥ ስርዓትን ለመተግበር አማራጭ ማድረጉን አስታውሰው ያለውን የአፈጻጸም ልዩነት ለልዑካን ቡድኑ ገልጸዋል፡፡ የቢሮ ኃላፊው አክለውም አሁን ላይ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ትግበራ የሚገኙበትን ደረጃ እና የሄዱበትን የአሰራር ሂደት በማሳያነት አንስተው አብራርተዋል፡፡

በመቀጠልም ተሞክሮውን ለመውሰድ በቢሮ የተገኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ልዑክ በበኩሉ በአፈጻጸም ሂደቱ ግልጽነት ይሻሉ በሚሏቸው ጉዳዩች ዙሪያ ጥያቄዎችን ያነሱ እና ሀሳብ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎች የቢሮው ኃላፊውና የባለስልጣኑ የስራ ኃላፊዎች ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡

አያይዘውም በነበሩበት የትኛውም ሂደት የቢሮው የአፈጻጸም ሂደት እንዲሳለጥ ባለስልጣኑ ላበረከተው አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን በድጋሚ ችረዋል፡፡
ቢሮዉ ለeGP ሲስተም ትግበራ ያዘጋጀውን ሠርቨር እና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች ልዑኩ እንዲጎኘዉ በማድረግ መረሃ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡