ባለስልጣኑ የ“ህብር ቀን”ን ከዝቅተኛ ተከፋይ ሰራተኞች ጋር አከበረ።

(ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም| አዲስ አበባ) – የፌደራል የመንግስት ግዥ እና ንብረት ባለስልጣን “የህብር ቀን”ን እና የ2019 አዲስ አመትን አስመልክቶ ከተቋሙ ዝቅተኛ ተከፋይ ሰራተኞች ጋር ያከበረ ሲሆን ለሰራተኞቹም ልዩ ልዩ ስጦታዎችን አበርክቷል።
ባለስልጣኑ በክረምቱ ወራት የተለያዩ ማህበራዊ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን በተለይም በሜቄዶኒያ የአረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል በመገኘት የምገባ መርሃ ግብር ማካሄዱ እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን የቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤት ግንባታ ማስጀመሩ ካከናወናቸው ማህበራዊ ሀላፊነቶች በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በንግግራቸው መተሳሰብ፣ መተጋገዝ እና መተባበር የቆየና የጠነከረ ኢትዮጵያዊ እሴት መሆኑን አውስተዋል። አክለውም ሰራተኞቹ የደመወዛቸው ዝቅተኛ መሆን ሳይገድባቸው ለተቋሙ ስኬት ላበረከቱት አስተዋጽዖ እና ላሳዩት የላቀ ትጋት የከበረ ምስጋና አቅርበዋል።
“እያንዳንዱ የተቋማችን ተግባር እርስ በእርስ የተሳሰረ በመሆኑ በቅንጅት ስንሰራ ውጤታማነታችን ይጎላል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ ተቋሙ ሁልጊዜም ቢሆን ከሰራተኞቹ ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም በመጪው 2019 አዲስ ዓመት ሰራተኞቹ የበለጠ በተነሳሽነት፣ በቅንነትና በታማኝነት አገልግሎት የሚሰጡበት የመተሳሰብና የስኬት ዘመን እንዲሆንላቸው የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።





0 Comments