የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በዲጂታል የመረጃት ስስር ላይ ምክክር አካሄዱ።

(ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም|አዲስ አበባ)፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ከግንባታ ባለሙያዎች፣ ኩባንያዎች እና ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የመረጃ ልውውጥና ትስስር መፍጠር በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ የጋራ የምክክር መድረክ አካሂደዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ እና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መስፍን ነገዎ (ዶ/ር) እንዲሁም የሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (INSA) ጋር በመተባበር ያበለጸገው «ዲጂታል የኮንስትራክሽን ሬጉላቶሪ ኢንፎርሜሽን ሲስተም» (Construction Regulatory Information System) ይዘት እና ሞጁሎች ላይ ገለጻ ቀርቦ ከመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስር ዓት ጋር መተሳሰር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጎበታል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት ተቋማቱ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ታግዘው የመረጃ ትስስር ማድረጋቸው የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ የሚደረገውን ጉዞ ከማፋጥን እንዲሁም የተገልጋዮችን አላስፈላጊ ወጪና እንግልት ከመቀነስ አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚኖረው ከመሆኑም በላይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውልና የግንባታ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል ብለዋል።
ሁለቱ ተቋማት በተለይም በዲጂታል ሥርዓት ደረጃ ሊለዋወጧቸው የሚገቡ አስፈላጊ፣ ወቅታዊና ተዓማኒ መረጃዎች ላይ ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በቀጣይም በጋራ የሥራ ሂደት የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን ይበልጥ ለማዳበርና ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የመንግሥት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱን (e-GP) ከተለያዩ የመንግሥትና የቁጥጥር ተቋማት ዲጂታል ሲስተሞች ጋር በማስተሳሰር የአገልግሎት ጥራትንና ግልጽነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።




0 Comments