በፌዴራል መንግስት የተያዙ የልማት ድርጅቶች የግዥ መመሪያ 1070/2017 ላይ ስልጠና እና የውይይት መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
(ነሐሴ 26/2017 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በፌዴራል መንግስት ከተያዙ የልማት ድርጅቶች ጋር የግዥ አፈጻጸም እና የንብረት አያያዝን በሚመለከት ውይይት እያደረገ ይገኛል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ታዓማኒ፣ አካታች እና ጥራት ያለው ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የግዥ አዋጁን ከማሻሻል ጀምሮ የፌዴራል ግዥ መመሪያን፣ የፌዴራል ንብረት መመሪያን፣ በፌዴራል መንግስት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች ግዥ መመሪያን እና የመድሐኒትና የህክምና ቁሳቁሶች መመሪያን በማውጣት ስራ ላይ እንዲውሉ አድርጓል።
በአዋጅ 1333/2016 ከተካተቱ አበይት ተግባራት አንዱ በፌዴራል መንግስት የተያዙ የልማት ድርጅቶች ግዛቸውን በኤሌክትሮኒክ ስርዓት እንዲፈጽሙ የሚያስችል ሲሆን የግዥ መመሪያውም የስራ ባህሪያቸውን መሰረት ያደረግ እንዲሆን የማድረግ ስራ ተሰርቷል።
ይህን ተከትሎም የልማት ድርጅቶች ውጤታማ የግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓት ሊገነቡ በሚችሉበት እና መመሪያውን ውጤታማ በሆነ መንገድ ሊፈጽሙ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት እየተደረገ ይገኛል።
የውይይት መነሻ ጽሁፍ እና በ2017 በጀት ዓመት የተተገበሩ አበይት ክንውኖችን ለውይይት ያቀረቡት የግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ውጤታማ የግዥ እቅድ ለውጤታማ ስራ ክንውን መሰረት መሆኑን ያብራሩ ሲሆን ግዥ ያለ እቅድ መፈጸም እንደሌልበትም አብራርተዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ አካታችነትን በማስፈን፣ ግልጽ የአሰራር ስርዓትን በመፈጠር፣ የተሳታፊን ቁጥር በመጨመር፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው የግዥ ሂደትን እውን በማድረግ በኩል ችግር ፈቺ ስርዓት መሆኑን አመላክተዋል።
የክብርት ወ/ሮ መሰረትን ገለጻ ተከትሎ በፌዴራል መንግስት ባለቤትነት የተያዙ የልማት ድርጅቶች የግዥ መመሪያ 1070/2017 ላይ በአቶ ገብያው ይታይህ እና በወ/ሮ አየናቸው ቸርነት ስልጠና እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን ስልጠናውም ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።








