Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

Author: Yonas Habesha

ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

(ነሐሴ 11/2017 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ለአመራርና ለሰራተኞች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቋል። ስልጠናው በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 እና በፌዴራል መንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ያተኮረ ሲሆን ዋና ዓላማውም አመራርና ሠራተኞች መመሪያዎችን አውቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና በመመሪያዎች ላይ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖሯቸው ብሎም  ችግሮችን የመፍታት አቅም እንዲዳብሩ ለማስቻል ነው።

በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 ላይ ስልጠና የሰጡት በኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም  ግንባታ ዴስክ ኃላፊ አቶ ናትናኤል አስፋው ሲሆኑ አዲሱ መመሪያ ቀድሞ ከነበረው መመሪያ በብዙ መንገዶች የተለዬ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አቶ ናትናኤል በገለጻቸው የግዥ መርሆች ከ5 ወደ 7 ከፍ የተደረጉ መሆናቸውን እነዚህም የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም ማስገኘት፣ በተወዳዳሪዎችና ተጫራቾች መካከል አድሎዎ አለማድረግ፣ ግልጽነትና ፍትሐዊነት፣ ግዥው በአካባቢ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የማያስከትል እንዲሁም የህይወት ዘመን ወጪን ትንተናን ከግምት ያስገባ እና መልሶ መጠቀምን የሚያበረታታ፣ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና ወጪ ቆጣቢ የሆነ፣ የግዥ አፈጻጸም ተግባራትን በታማኝነት መፈጸም፣ በግዥ አፈጻጸም ሂደት የሚሰጡ ውሳኔዎችና የሚወሰዱ እርምጃዎች ተጠያቂነት የሚያስከትሉ መሆናቸው፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራን ማበረታት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ አቶ ናትናኤል አያይዘውም አዲሱ መመሪያ የስራ ፈጠራን የሚያበረታታና አዳዲስ የግዥ ስልቶች የተካተቱበት እንዲሁም የተጋነነና የተሰበረ ዋጋ በመቶኛ የመወሰነ መሆኑን ያብራሩ ሲሆን መመሪያውን ማንበብ፣ ማወቅና ማሳወቅ የተቋሙ አመራርና ሰራትገኛ ሀላፊነት ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡:

በፌዴራል መንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ላይ ስልጠና የሰጡት በኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት እቅድና መረጃ ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዘበነ ገዛኸ በበኩላቸው አዲሱ የንብረት አስተዳደር መመሪያ ተለምዷዊ አሰራርን በማስቀረትና ዲጂታል አሰራርን በማስፈን በኩል ትልቅ ለውጥ ያመጣ ነው ያሉ ሲሆን ንብረትን በእቅድ መምራት፣ ንብረትን በአግባቡ ይዞ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ማድረግ፣ የንብረት አወጋገድን በአግባቡ ማከናወን እና በግንባታ ላይ ያሉ ንብረቶች የንብረት ስራ ክፍል ክትትል ማድረግ እንዲሚጠበቅበት መመሪያው እንደሚያስገነዝብ አብራርተዋል፡፡

ከስልጠናው በኋላ ውይይት የተደረገ ሲሆን ለተጠየቁት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያን ተሰጥቶ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡

መፍትሔ ሰጪ መሪ ለመሆን የተቋሙን አሰራር እና የአሰራር ስርዓቶች ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ

(ነሐሴ 09/2017 ዓ/ም)፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዘመናዊ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓት በማጠናከር በ2022 ዓ/ም በአፍሪካ አርዓያ ከሆኑ ተቋማት አንዱ የመሆን ርዕይን ሰንቆ በትጋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ በዚህም አዋጁን ማሻሻል ጨምሮ ከ20 በላይ መመሪያዎችን ተግባራዊ አድርጓል፡፡

በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራሩና ሰራተኞች መመሪያዎችን አውቀው እንዲተገብሩ ለማስቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡ በስልጠናው ላይ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳየሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት እንደገለጹት መፍትሔ ሰጪ እና አገልጋይ መሪ ለመሆን የተቋሙን አሰራር እና የአሰራር ስርዓቶች ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም የግዥ አፈጻጸምና የንብረት አስተዳደር መመሪያዎችን አውቆ ለመተግበር ስልጠና መስጠቱ አስፈልጓል ብለዋል፡፡

የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ላይ ስልጠና እየሰጡ የሚገኙት አቶ ናትናኤል አስፋው በበኩላቸው በተቋሙ ውስጥ ውጤታማ ስራ ለማከናወን የተቋሙን የጋራ እሴት የሆነውን ርዕይ ማወቅና ስራዎችን ከተቋሙ ርዕይ አንጻር መፈጸም ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በስልጠናው ስራ አስፈጻሚዎች፣ ዴስክ ሀላፊዎች፣ ቡድን መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን ስልጠናው እስከ ነሐሴ 11/2017 ዓ/ም የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የእውቅና እና የምስጋና መርሃግብር ተካሄደ።

(ነሐሴ 05/2017 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን አዘምኖ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ አገልግሎት ለመስጠት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ከእነዚህ ውስጥ አዋጁን ማሻሻል ዋነኛው የለውጥ መነሻ ሲሆን አዋጁን ተከትሎምም መመሪያዎችና ማስፈፀሚያ ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ወደ ትግበራ ተግብቷል።

በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በመመሪያ ዝግጁቱ ላይ ለተሳተፉና ለለውጡ ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ለነበራቸው ተቋማት፣ አመራርና ባለሙያዎች እውቅና ሰጥቷል።

በእውቅና እና በምስጋና መርሃግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈቃዱ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም መሰል መመሪያዎች የሚዘጋጁት በአማካሪ በመሆኑ ብዙ ገንዘብ ያስወጣ የነበረ ሲሆን አዋጁን ተከትሎ የወጡ መመሪያዎች በውስጥ አቅም ብሎም አሳታፊ በሆነ መልኩ ስለተዘጋጁ ወጪን ማዳን መቻሉ እንደተጠበቀ ሆኖ የመመሪያዎች ጥራትም ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው የመመሪያ ዝግጅት ስራው እጅግ አድካሚ የነበረ ቢሆንም  ሳትሳሱ ያለምንም ክፍያ እውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን እና ጉልበታችሁን  ለተቋማችን ስለሰጣችሁ ምስጋና ይገባችኋል፤ ወደፊትም አብረን ሆነን ብዙ ለውጦችን እናመጣለን ብለዋል።

ለምለሟ ምስራቅ ጉራጌ ሌላ ገፀ በረከት ተደረበላት።

(ሀምሌ 26/2017 ዓ/ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በክረምት ወራት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ሲያከናውን የቆዬ ሲሆን በዛሬው እለት የባለስልጣኑ አመራርና ሠራተኞች  በምስራቅ ጉራጌ ዞን ቡኢ ከተማ ከ25000 በላይ ችግኞችን ተክለዋል።

በእለቱ ከችግኝ ተከላው በተጨማሪ ለ100 ተማሪዎች ሙሉ የመማሪያ ቁሳቁስ አበርክተዋል። በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ሀሰንን ጨምሮ የዞን፣ የወረዳ እና የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

ከችግኝ ተከላው በኋላ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ኢኮሎጂን ለማስተካከልና የቱሪዝም ምህዳርን ለማስፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው ያመላከቱ ሲሆን ዞኑ በትኩረት እየሰራ እንደሆነ አመላክተዋል።

የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው በክረምቱ ወራት በመትከል ማንሰራራት በሚል መሪ ቃል ችግኞች ሲተከሉ መቆየታቸዉን ጠቅሰው በዛሬዉ እለትም ከ25000 በላይ ችግኞችን ተክለናል ብለዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም ጉራጌ የሰላምና የታታሪነት ተምሳሌት የሆነ ማህበረሰብ መክተሚያ በመሆኗ በዚህ ቦታ አሻራችን በማሳረፋችን ደስ ይለናል ያሉ ሲሆን ችግኞችን ከመትከል በዘለለ የመንከባከብ ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

በመጨረሻም የባለስልጣኑ አመራሮች የትምህርት ቁሳቁሶችን ለተማሪዎች ያበረከቱ ሲሆን ለባለስልጣኑ አመራርም ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የተለያዩ ስጦታዎች ተበርክቶላቸዋል።