Skip to contentSkip to main navigation Skip to footer

Author: Yonas Habesha

የገንዘብ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት ሩብ አመት አፈጻጸምን ገመገሙ።

(ጥቅምት 04/2018 ዓ.ም)፣ የገንዘብ ሚኒስቴርና በገንዘብ ሚኒስቴር ስር የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈጻጸምን በጋራ ገምግመዋል።

በግምገማው ወቅት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈጻጸም በዋና ዳይሬክተሯ ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የቀረበ ሲሆን በሩብ ዓመቱ መመሪያዎች፣ የስልጠና ሞጁሎች እና መሰል የአሰራር ስርዓቶች የተዘረጉበትና ወደ ትግበራ የተገባበት መሆኑን አመላክተዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የአሰራር ስርዓቱን ሙሉ ለሙሉ ዲጂታላይዝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ የሰራ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) በሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ተግባራዊ መደረጉን፣ ዲጂታል ትምህርት (E- learning) መዘጋጀቱን፣ የኤሌክትሮኒክ ትምህርቱ አዳዲስ መመሪያዎችን እንዲያካትት መደረጉን፣ ዲጂታል የደብዳቤ መጻጻፊያ ተገባራዊ መደርጉን፣ ዲጂታል የአስተያየት መስጫ እና የቅሬታ መቀበያ ስርዓቶች  ተግባራዊ መደረጋቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አክለውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ሥርዓት ትግበራን ወደ ክልሎች ለማውረድ ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝና በዚህ ሩብ ዓመት ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ ለሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንዲሁም ለሌሎች ክልሎች አስፈላጊውን ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ እና የመሰረተ ልማት ተግባራት እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በተጨማሪም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ከሌሎች ሲሲተሞች ጋር የማስተሳሰር ስራ መሰራቱንና የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥን (e-GP) ስርዓት በኢንሳ የደህንነት ኦዲት እንደተደረገለት በማብራሪያቸው የተካተተ ሲሆን የተጠናከረ ኦዲትና ክትትል ስርዓት መዘርጋቱንም በገለጻቸው አንስተዋል።

የመንግስት ግዥና ንብረት ህጋዊነት ኦዲት የመንግስትን በጀት በአግባቡ እንድንጠቀምና በጀቱ ከታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውል በማድረግ ረገድ ያለው ሚና የጎላ ነው፡፡ አቶ አዲስ ጎዳና

(ጥቅምት 26/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ሥርዓትና ቁጥጥርን በማጠናከር ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም እንዲያስገኝ የማስቻል ተልዕኮን ይዞ በከፍተኛ ትጋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ባለስልጣኑ ይህን ተልዕኮን ለመወጣት የአሰራር ስርዓቶችን ከመዘርጋት ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ ተገልጋዮችንና ባለድርሻ አካላትን እያሰለጠና የጋራ ተግባቦት እንዲኖር ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ባለፉት ሁለት ቀናት  ከክልል የግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቶች  ለተውጣጡ ባለሙያዎች እና ለባለስልጣኑ የኦዲት ባለሙያዎች በመንግስት ግዥና ንብረት ህጋዊነት ኦዲት ላይ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥ እና ንብረት አፈጻጸም እና ህጋዊነት ኦዲት እና ክትትል መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ አዲስ ጎዳና ሲሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ህጋዊነት ኦዲት ተቋማት የመንግስትን በጀት በአግባቡ እንዲጠቀሙና በጀቱ ከታለመለት ዓላማ ላይ እንዲውል በማድረግ በኩል ያለው ሚና የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

አቶ አዲስ በስልጠናቸው የግዥ ኦዲት በተቋማት ላይ የህዝብ አመኔታን እንዲሰፍን ለማድረግ፣ የተቋማትን የግዥና ንብረት አፈጻጸም ጥራትን ለማሳደግ፣ የህግ ተገዥነትን ለማስፈን፣ ብልሹ አሰራርን ለመከላከልና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ዋጋ ለማስገኘት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አቶ አዲስ አክለውም አንድ የኦዲት ባለሙያ ስራውን በሚፈለገው ልክና በትክክለኛው መንገድ ለማከናወን ወደ ኦዲት ስራ ከመግባቱ አስቀድሞ የግዥ ኦዲት መርሆችን ማወቅና መላበስ ይኖርበታል ሲሉ በአስንዖት የገለጹ ሲሆኑ እነዚህም ህጋዊነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ለገንዘብ ዋጋ መስጠት፣ ፍትሃዊነት፣ ታማኝነት፣ ተጨባጭነት፣ ነፃነት እና ሙያዊነት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

ስልጠናው በተጨማሪም የኦዲት መነሻና መድረሻ፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች እና ሊወሰዱ የሚገባቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ያካተተ ነበር፡፡

በመመሪያዎች ላይ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

(ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በአዋጅ 1333/2016 የተሰጠውን ተግባርና ሀላፊነት ለመወጣት የአዋጅ ማስፈጸሚያ መመሪያዎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ከማዘጋጀት ባለፈ  መመሪያዎችንና የአሰራር ስርዓቶችን ተገልጋዩ ማህበረሰብ አውቆና ተረድቶ እንዲፈጽማቸው ለማስቻል ተከታታይ ስልጠናዎችን እየሰጠና ውይይቶችን እያካሄደ ይገኛል።

 በዚህም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከጥቅምት 19-21/2018 ዓ.ም ለፌዴራል ተቋማት የህግ፣ የስነ መግባር እና የውስጥ ኦዲት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 እና በፌዴራል መንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ላይ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቋል።

በፌዴራል መንግስት የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 1073/2017 ላይ ስልጠና የተሰጠው በኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም  ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ እና ወ/ሮ ወገኔ አይሸሽም ሲሆን  አዲሱ መመሪያ ቀድሞ ከነበረው መመሪያ በብዙ መንገዶች የተለዬ መሆኑ ተብራርቷል። አቶ መላኩ በገለጻቸው በቀድሞ የግዥ መመሪያ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ለአዲሱ የግዥ መመሪያ ዝግጅት ግብዓት ማድረግ እንደተቻለና መመሪያው የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፈተኛ ዋጋ እንዲያስገኝ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በፌዴራል የመንግስት የንብረት አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 1095/2017 ላይ ስልጠና የሰጡት በኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት እቅድና መረጃ ዴስክ ሀላፊ የሆኑት አቶ ዘበነ ገዛኸ ሲሆኑ አዲሱ የንብረት አስተዳደር መመሪያ ተለምዷዊ አሰራርን በማስቀረትና ዲጂታል አሰራርን በማስፈን በኩል ትልቅ ለውጥ የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል። አቶ ዘበነ በማብራሪያቸው ንብረትን በእቅድ መምራት፣ ንብረትን በአግባቡ ይዞ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውል ማድረግ፣ የንብረት አወጋገድን በአግባቡ ማከናወን እና በግንባታ ላይ ያሉ ንብረቶች የንብረት ስራ ክፍል ክትትል ማድረግ እንዲሚጠበቅበት መመሪያው እንደሚያስገነዝብና ሁሉም በየተሰጠው የስራ ሀላፊነት ልክ ንብረቶችን መያዝና መጠበቅ እንደሚገባው አብራርተዋል፡፡

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከአምራች ኢንዱስትሪው ጋር የውይይት አካሄደ።

(ጥቅምት 17/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመንግስት ግዥ ስርዓት ለአምራች ኢንዱስትሪው የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በሚመለከት ከአምራች ኢንዱስትሪ አመራር ጋር ውይይት አካሂዷል። ውይይቱ የግዥ ስርዓቱ ለአምራች ኢንዱስትሪው የፈጠረውን እድል በመጠቀም የሀገረ በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎችን አቅም ማጎልብትና የገብያ ትሥስር መፍጠርን ያለመ ነው።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች አንዱ የሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪን ማብረታታትና አቅም ማጎልበት እንዲሁም ገቢ ምርትን እንዲይተኩ ማስቻል መሆኑን ሲሆን ለዚህም ለሀገር በቀል ኢንዱስትሪው የሚያበረታታ የግዥ ስርዓት ተፈጥሯል ብለዋል። ክቡር አቶ መላኩ አያይዘውም የተፈጠረውን የግዥ እድል በአግባቡ ለመጠቀም አደረጃጀትን ማጠናከር፣ ባለሙያዎችን በእውቀትና በክሎት ማላቅ እንዲሁም በጥራትና በብዛት ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

በሌላ በኩል የውይይቱን መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ሲሆኑ የሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪውን ለመደገፍና ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች እንደተዘጋጁና የሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ የመንግስትን ግዥ መደገፍ መሆኑን አመላክተዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት በተለይም በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አዋጅ 1333/2016 እና እሱን ለማስፈጸም በወጡ የህግ ማዕቀፎች ሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪውን የሚያበረታቱ፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የሚያሳድጉ እና ውድድርን የሚጨምሩ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የገበያ ትሥስር በመፈጠርና ውጤታማ የአምራች -ተጠቃሚ ሰንሰለትን በማጠናከር በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ትልቅ ሚና እንዳለውና አምራች ኢንዱስትሪዎች ከማምረት በተጨማሪም በአሉብት ሆነው በአራቢነት መስራት እንደሚችሉም ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጸዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው በተለይም እሴትን ጨምረው ለሚያመርቱ ሀገር በቀል አምራች ኢንዱስትሪዎች በጨመሩት እሴት ልክ ልዩ አስተያየት የሚያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል። እንደ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ገልጻ በግዥ ስርዓት የልዩ አስተያየት ዋና ዋና አላማዎች መንግስት የጀመረውን የኢኮኖሚ ሪፎርም ዕውን ለማድረግ፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት፣ ልዩ ድጋፍ ለሚፈልጉ የህብረተሰብ ክፍሎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እና የሀገር ውስጥ ምርትን የመጠቀም ባህልን ለማጎልበት መሆኑ ተጠቁሟል።

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በክቡር ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበልና በዋና ዳይሬክተሯ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ምላሽና ማብራሪያ መደረኩ ፍጻሜውን አግኝቷል።