Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ነው፦ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን

(መስከረም 08/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) በሚተገበርበት ሁኔታ ላይ ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

በውይይቱ ወቅት ባለስልጣኑ የግዥ ሂድቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ የመንግስት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ዋጋ እንዲያስገኝ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ አብራርተዋል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት አያይዘውም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት የግዥ ሂደቱን ከእጅ ንክኪ ነጻ በማድረግ፣ ተደራሽነትን በማስፋት፣ አሳታፊነትን በመጨመር፣ ወጪን በመቀነስ እና ግልጸኝነትን በማስፈን በኩል ያለው አስተዋጽዖ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው ሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ግዣቸውን በዚህ ስርዓት እየፈጸሙ የሚገኙ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማ መስተዳደርና ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ስድስት ክልሎች ወደ ትገበራ እየገቡ እንደሚገኙ እንዲሁም ሌሎች ክልሎችም ስርዓቱን እንዲተገብሩት ለማስቻል ተከታታይ ውይይቶች እየተደረገና ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (e-GP) ስርዓት በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ስርዓት ነው ሲሉ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ክቡር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገልጸዋል። ‎

‎የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን መንግሥት በተቋማት ሪፎርም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰው በግዥ ስርዓቱ እየተደረገ ያለው ሪፎርም አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘውም ‎የግዥ ስርዓቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ በግዥ ሂደት ውስጥ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን የክልሉ መንግሥት የኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኑንና ለዚሁ የሚያግዝ አዋጅ መጽደቁን አመላክተዋል።

በመጨረሻም ስርዓቱን ተግብሮ ለማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን ክልሉ ወደ ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዥ ስርዓት ለመግባት በሚያደረገው ጥረት የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ድጋፉን እንዲያጠናክርም ርዕሰ መስተዳደሩ አሳስበዋል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *