በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከሁሉም የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች ጋር ውይይት ተካሄደ።
(ሰኔ 17/2017 ዓ.ም)፣ የፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከሁሉም የፌደራል ባለበጀት መ/ቤቶች የሥራ ኃላፊዎች እና የግዥና ንብረት ኃላፊዎች ጋር የ2017 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀም ዙሪያ በጋራ ለመገምገም እና የቀጣይ በጀት ዓመት ዕቅድን የጋራ ለማድረግ በማለም የተዘጋጀ መድረክ ነው ።
የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይት የሪፎርም ስራዎች፣ አዲሱን አዋጅ 1333/2016 ተከትሎ የወጡ የህግ ማዕቀፍ ዝግጅትና ማሻሻያ ሥራዎችና የተካተቱ መሠረታዊ ለውጦች፣ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓቱን ወደ ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች ከማውረድ ጋር የተያያዙ ተግባራት፣ የተዘጋጁና ጸድቀው ተግባር ላይ የዋሉ መመሪያዎች፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ጥራትና ቅልጥፍናን ለመጨመር የተተገበሩ የዲጅታል ስራዎች በተለይም የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ (ኢጅፒ) ትግበራን ይበልጥ ለማሳለጥ የተሻሻሉ ትግበራዎችና የሲስተሙ ጠቀሜታዎችና አዋጭነት ፣ የቅንጅታዊ አሰራር ውጤታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች፣ የተሠጡ ስልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎችና የተገኙ ውጤቶች በስፋት ተተንትነው ቀርበዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አያይዘውም የ2018 በጀት ዓመት እቅድን ያቀረቡ ሲሆን እቅዱ የ2017 በጀት ዓመት ክንውንን መነሻ ያደረገና የተገኙ መልካም ውጤቶችን የምናስቀጥልበት በሌላ በኩል የነበሩብንን ክፍተቶች የምንሞላበት እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በኢ.ጂ.ፒ ሲስተም ትግበራ ዙሪያ የተደረጉ ማሻሻያዎች በአቶ እውነቱ አበራ (የኢ.ጂ.ፒ. ሲስተም አልሚና የፔራጎ ሥራ አሰኪያጅ ) የቀረበ ሲሆን ፣ በውስጥ አቅም ለምተው ስራ ላይ የዋሉ ዲጂታል ስራዎች (website, e- learning, letter management, …) በኢጂፒ ፕሮጀክት የአፕሊኬሽን ቲም ባለሞያ አቶ ኃይለሚካኤል ገብሩ አማካኝነት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመጨረሻም የቀረቡትን ገለፃዎችን መነሻ በማድረግ ከመድረክ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ምላሽና ተቋማዊ የማጠቃለያ እና የቀጣይ የጋራ ስራ አቅጣጫዎችና የባለስልጣኑን የመተግበር ዝግጁነት በመግለጽ የዕለቱ መርሃ-ግብር ተጠናቋል።










0 Comments