በቁልፍ የግዥ አፈጻጸም፣በክልል የወረዳ ግዥ ኦዲትና በካልም ኦዲት ዙሪያ ዉይይት ተካሄደ፡፡
(ግንቦት10/2017ዓ/ም) ባለስልጣኑ ላለፉት ሁለት ቀናት በደብረዘይት ከተማ ፒራሚድ ሆቴልና ሪዞርት ከክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ዉይይት ለማድረግ ከያዛቸዉ አጀንዳዎች ዉስጥ አንዱና የመጨረሻዉ የሆነዉ ቁልፍ የግዥ አፈጻጸም አመላካቾች (KPI) ዙሪያ የ2016ዓ/ም አፈጻጸምን የሚዳስስና የተሻለ የተገበሩ ክልሎች ተሞክሯቸዉን የሚያጋሩበት ብሎም የወረዳ ግዥ ኦዲትና የካልም (KALM) ወረዳዎች ኦዲት የአፈጻጸም ሪፖርት የሚቀርብበት መርሃ-ግብር ነዉ፡፡
አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥ ፕሮጀክት አስተባባሪ ጥቅል ሪፖርቱን ያቀረቡ ሲሆን የክልሎችን አፈጻጸም በንጽጽር በማመላከት አፈጻጸማቸዉ የተሻለዉን በተሞክሮነት እንዲወስዱና ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸዉ ደግሞ መሻሻል እንዲችሉ ዕድል በሚሰጥ መልኩ አቅርበዋል፡፡
አስተባባሪዉ ከግዥ ኦዲት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ባደረሱበት ወቅት የኦዲት ዋነኛ ዓላማ የተከናወኑ ተግባራት ትክክለኛዉንና የተናበበዉን ሂደት ተከትለዉ መተግበራቸዉን ለማረጋገጥና ስህተት በተፈጠረ ጊዜም ተጨማሪ የማስተካከያ ዕድል ለመስጠት የሚያሥችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አክልዉም ከየወረዳዎቹ የሚላኩ የኦዲት ሪፖርቶች የተገኘዉን ዉጤት ብቻ ሳይሆን አስቻይ ሁኔታዎችን፣ለሚያጋጥሟቸዉ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችንና ግብረ-መልሶችን ሊያካትቱ እንደሚገባና የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታን ባገናዘበና በሚመጥን መንገድ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ተሳታፊዎች ሃሳብ አስተያየታቸዉን በሰጡበት ወቅት ለሰነድ ዝግጅቱና ለአቀራረቡ ብሎም ባለስልጣኑ ለትግበራዉ ላሳየዉ ቁርጠኝነት ያላቸዉን አድናቆት በማስቀደም ከKPI ሲስተም ምዝገባ፣ከቢሮ ኃላፊዎች ትኩረት ማነስና ከ ማጽደቅ( Approval) ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ምላሽ ከሚሹት ጎራ አንስተዋል፡፡
ለተነሱ ጉዳዮች የፕሮጀክት አስተባባሪዉን ጨምሮ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ ማጠቃለያ የሰጡ ሲሆን ዘርፉ ከልማት እንቅስቃሴዎች ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለዉ ስለሆነ በተለይም ለቁልፍ የግዥ አመላካቾች በቂ ትኩረት በመስጠት ሊተገበር እንደሚገባ እና የ2017ዓ/ም ሪፖርት ወቅቱን ጠብቆ እንዲላክ የተገለጸ ሲሆን ባለስልጣኑ በማንኛዉም የትግበራ ሂደት የተለመደ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ መርሃ-ግብሩ ተጠናቅቋል፡፡







0 Comments