Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት(e-GP) በደቡብ ምዕራብ ክልል ለመተግበር  ስምምነት ተደረገ።

(ግንቦት 18ቀን 2017 ዓ.ም) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ፋይናንስ ቢሮ እና በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን መካከል የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን በክልሉ በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች  ለመተግበር  ስምምነት ተደረገ፡፡

በአዲሰአበባ ኃይሌ ግራንድ ሆቴል በተዘጋጀው የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የፌዴራል የመንግስት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት በሁሉም የፌዴራል መ/ቤቶችና ቅርንጫፎቻቸው እየተተገበረ መሆኑን አንስተዉ  ስርዓቱን መተግበር ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን፣ ብልሹ አሠራርን በማስወገድ፣ በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ፤ በፋይናንስ አሰራር ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ለማስወገድ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

አያይዘዉም የመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን በፌደራል ብቻ ሳይሆን በሌሎች ክልሎች ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በራስ ተነሳሽነት ተቀብሎ ለመተግበር  መዘጋጀቱ የዘመነ የፋይናንስ አሰራር ለመከተል ያለዉን ከፍተኛ ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።

በክልሉ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲቻል ከ2018ዓም በጀት ዓመት ጀምሮ ለተመረጡ ቢሮዎች ባለሞያወች በባለሥልጣን መ/ቤቱ በኩል ስልጠናዎችና ሌሎች አስፈላጊ ቴክኒካል ድጋፎች እንደሚደረግላቸዉ ገልፀዋል፡፡

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊዋ ክብርት ወሠነች ቶማስ እንዳሉት፤ የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት በክልሉ ግዥ በሚፈጽሙ በተመረጡ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚተገበር መሆኑን አስታውሰው ስርዓቱ የሚባክኑ ሀብቶች ለማዳን የሚያስችል ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑን አንስተው፤ የፋይናንስ ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን በማስፈን በህዝብና መንግስት መካከል መተማመን እንደሚያጎልብት መገንዘባቸውን አስረድተዋል።

አክለውም በተለይም በመንግስት መስሪያ ቤቶች ከጨረታ ሂደት ጋር በተያያዘ ያለውን የወረቀት ንክኪ፣ የጊዜና የጉልበት እንዲሁም አለአግባብ የሚወጡ ወጪዎችን ማስቀረት የሚያስችል አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።

አያይዘውም ክልሉ በቅርብ የተመሠረተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተለይም ከመሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ ውስንነቶች እንደሚገጥሙ አንስተው ለአስቻይ ሁኔታዎች ከመስተዳድሩ ጋር በግልጽ መነጋገርና ለትግበራው በሙሉ ዝግጂነት መግባት እንደሚያስፈልግ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸው ባለስልጣኑ ወደ ሲስተሙ እንዲገቡ ለፈጠረላቸው መነቃቃት ምስጋናቸውን በማስቀደም ቀጣይም የተለመደ ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

አጠቃላይ ስለ ኢጅፒ ሲስተሙ ሙሉ ገለጻ እንዲሰጡ በስፍራዉ የተገኙትና ሲስተሙን ያለሙት የፔራጎ ኢንፎርሜሽን ኃ.የተ.ግ.ማ. የተሰኘው የሶፋትዌር ድርጅት ሃላፊ አቶ እውነቱ አበራ፤ ዘመናዊና ቀልጣፋ የፋይናንስ አሰራር መዘርጋት የሚያስችል ሶፋትዌር መሆኑን አንስተዉ፤ ይህም በመንግስት ግዥ የሚወዳደሩ ተቋማት ያለቦታ ገደብ እኩል በሆነ አሰራር ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የግዥ ህግ በአግባቡ እንዲተገበር፣ የጊዜና ጉልበት ብክነት ከመቀነስ ባለፈ ከተለያዩ አማራጮች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለጨረታና መሰል ግዥዎች ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚያስቀር መሆኑን አመላክተዋል።

በመጨረሻም ሲስተሙን ለመጀመር ያለውን የተሻለ አማራጭና አስቻይ ሁኔታዎች የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር የገለጹ ሲሆን ክልሉ በአጭር ጊዜ ላሳየው ቁርጠኝነት ልባዊ ምስጋናቸውን በድጋሜ ችረዋል። ባለስልጣኑ ለየትኛውም ሙያዊ ድጋፍ ያለውን ዝግጁነትም አሳይተዋል።

በመጨረሻም ሲስተሙን ለመተግበር የሚያስችለውን የሥራ ስምምነት ሰነድ የክልሉ ፋይንናስ ቢሮ ከባለስልጣኑ ጋር ተፈራርሟል።

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *