Skip to content Skip to main navigation Skip to footer

በኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ሥርዓት ዙሪያ ከባንኮች እና ኢንሹራንሶች ጋር የውይይት መድረክ ተካሄደ፡፡

(ሰኔ 5/2017 ዓ/ም) ባለስልጣኑ በኤሌክትሮኒክ የመንግስት ግዥ ሥርዓት ዙሪያ በርካታ ተግባራትን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትስስር ተግባራዊ እያደረገ እና አሰራሩን ይበልጥ እያዘመነ ለዲጅታል ኢኮኖሚ ዘርፉ ሃገራዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባር እና ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል፡፡

ይህንን ተከትሎ ከባንኮች እና ኢንሹራንሶች ጋር በጋራ መስራት የሚገባ ተግባር በመሆኑ ቀደም ሲል ሲስተሙን አስተሳስሮ ለመተግበር ባለስልጣኑ መድረክ የፈጠረ ቢሆንም ተግባራዊነቱ ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ ዳግም ተወያይቶ ለትስስሩ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ታስቦ በካፒታል ሆቴል የተዘጋጀ መድረክ ነው፡፡

መድረኩን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ የከፈቱ ሲሆን ከመንግስት የኤሌክትሮኒክ ግዥ ሥርዓት ጋር ተያያዥ ገለጻ በመስጠት የግዥ ስርዓቱ የደረሰበትን አጠቃላይ ሁኔታ፣ ያስገኛቸው ጠቀሜታዎች፤በትግበራ ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና አስቻይ ሁኔታዎችን በገላጻቸዉ ወቅት አካተዋል፡፡

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂን የገለጻቸው አካል ያደረጉት ዋና ዳይሬክተሯ በዚህ ረገድ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ግንባር ቀደም ሚና ከሚጫወቱ ተቋማት መካከል መሆናቸውን አስታውሰው የዲጅታል ሽግግር ጉዞ ማሳያ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን የኤሌክትሮኒክ ግዥ አፈጻጸም ሥርዓትን በመተግበር ሂደት የሲስተም ትስስር ሊፈጥሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመቀጠልም በግዥ ሂደት ሲስተሙ የሚያተናግዳቸው ትግባራዎች በዝርዝር በማመላከት ከነዚህም መካከል መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል፤ከአቅራቢዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ተቋማት ጋር የሲስተም ትስስር መደረጉን አስታውሰው በቀጣይ በኢጂፒ ሲስተም በኩል ብቻ ግዥ መፈጸም እንዳለበት የሚደነግገው ህግ ተፈጻሚነት በማረጋገጥ በመንግስት ግዥ ላይ የሚስተዋለውን የውስንነት ችግር ለመፍታት እና ከእጂ ንክኪ የጸዳ ለማድረግ ብሎም ደህንነቱ የተጠበቀ የደንበኞችን እርካታ የሚያረጋግጥ የዘመነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ተገቢ ስለሆነ በትስሰር ሊተገበር እንደሚገባ ገልጸው ስርዓቱን ተጠቅመው ባንኮች እና ኢንሹራንሶች የሚያከናውኗቸውን ተግባራት በግልጽ ተገንዝበው በሲስተሙ መተግበር እንደሚገባቸው አብራርተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተራ በገለጻቸው በዚሁ የግዥ ስርዓት በርካታ የገንዘብ ቁጥር ያለዉ ግዥ የሚፈጸም እና በሂደቱም ዋስትና የሚጠየቅባቸው በሲስተሙ በፈሰሱ ጨረታዎች ልክ የሚሆንበት አሰራር በወረቀት ሊተገበር ስለማይገባ አስተማመኝ እና ደህንነቱ የተጠበቀ ዋስትና በሲስተም ሊታሰርለት ይገባል ብለዋል፡፡ ባንኮችና ኢንሹራንሶችም መሰል ጉዳዩችን በበይነ በርብ አለማድረጋቸው የተፈለገውን ዓላማ ከግብ ለማድረስ እንቅፍት ስለሆነ ይህን ተፈጻሚ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እና ሂደቶች ሳይዛነፉ እንዲተገበሩ ለማድረግ ውይይቱ ማስፈለጉን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም የሲስተም ትስስሩ በባንኮች እና ኢንሹራንሶች እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን የሲስተሙን ሂደት በግልጽ ያመላከተ ገለጻ በቪዲዩ በማስደገፍ በአልሚው ድርጅት/ፔራጎ/ ከፍተኛ ባለሙያ በአቶ ኤልያስ ጥበቡ አማካኝነት ለተሳታፊዎች ቀርቧል፡፡

የቀረበውን የውይይት መነሻ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ተሳታፊዎች አስተያየት የሰጡ ሲሆን ባለስልጠኑ የግዥ ስርዓቱን ለማዘመን የሄደበትን እርቀት አድንቀው የሲስተም ትስስሩን በተመለከተ በአዎንታዊ ጎኑ የተቀበሉት እና ለመተግበርም ዝግጁነታቸውን የገለጹ ሲሆን ተገቢውን ቴክኒካል ስልጠና ከማግኘት አንጻር፤ከደንበኞቻቸው የአገልግሎት መስጫ ማዕከል እና ሌሎች ቴክኒካል ጉዳዩች ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን ምላሽ በሚሹት ጎራ አንስተዋል፡፡

ለተነሱ ሃሳቦች ተቋማዊ ምላሽ የሰጡት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መስረት መስቀሌ በማጠቃለያቸዉ የመድረኩ ተሳታፊ ባንኮች እና ኢንሹራንሶች ትስስር ለመፍጠር ላሳዩት ፈቃደኝነት ልባዊ ምስጋናቸውን በመቸር በቀጣይ የስራ ውል ስምምነት በመፈራረም ወደ ትግበራ የሚገባ እና ፈጥነው ተግባራዊ የሚያደርጉ ባንኮችን እውቅና በመስጠት በሚዲያ ጭምር ለህዝብ ተደራሽ የሚሆንበት አሰራር እንደሚኖር አስታውሰው ፈጥኖ መተግበር ያለበት ጉዳይ በመሆኑ ባለስልጣኑ ባለሙያ በመመደብ በስፍራው አልያም በማዕከል ደረጃ ስልጠና ሰጥቶ በአጭር ቀናት ውስጥ ወደ ትግበራ እንደሚያስገባ እና ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም በአሰራሩ ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ የማንዋል መረጃ የማንቀበል በመሆኑ ማንኛውም ግዥ ፈጻሚ መ/ቤት የማንዋል ዋስትናን የማይቀበልበት አሰራር ይዘረጋል ፣ በሂደትም አስገዳጅ ሆኖ ሲስተሙ ራሱ የሚዘጋበት ሂደትን በማካተት የሚተገበር በመሆኑ ይህንን ተገንዝበን ለተግባራዊነቱ ዝግጁ ልንሆን ይገባል በማለት የውይይቱን መርሃ-ግብር አጠናቅቀዋል፡፡

0 Comments

There are no comments yet

Leave a comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *