በመንግስት የልማት ድርጅቶች ደረጃ የመጀመሪያው ስልጠና መስጠት ተጀመረ።
(ሰኔ 03/2017 ዓ.ም) የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአሰራር ስርዓቱን አዘምኖ በ2022 በአፍሪካ ግንባር ቀደም የመንግስት ግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም የመሆን ራዕይን ሰንቆ በትጋት እየሰራ የሚገኝ ተቋም ነው።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተለይም ስራዎችን በማዘመን፣ ጥራት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስርዓትን ከማላመድ ተነስቶ የተቋማት ባህል እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፤ ተጨባጭ ለውጦችንም አስመዝግቧል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት 169 የፌዴራል ተቋማት እና 93 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ግዣቸውን በዚህ ስርዓት እንዲፈጽሙ ያደረገ ሲሆን ከተማ መስተዳደሮችና ክልሎችም ስርዓቱን እንዲተገበሩት ለማስቻል ስልጠና እየሰጠና ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ይህ እንደተጠበቀ በፌዴራል መንግስት የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን የስርሻቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ተቋማቱን ያሳተፈ አዲስ መመሪያ ጸድቆ ወደ ስራ ተገብቷል።
በፌዴራል መንግስት ስር የሚተዳደሩ የልማት ድርጅቶችን አዲሱ መመሪያ የልማት ድርጅቶች የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ ስርዓትን እንዲተገብሩ የሚያስችል በመሆኑ በልማት ድርጅቶች ረገድ የመጀመሪያው ስልጠና ለኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩብ እየተሰጠ ይገኛል።
ስልጠናው ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) ስርዓት ምንነት፣ አተገባበር እና ፋይዳ እንዲሁም የመንግስት ግዥና ንብረት አዲሱ አዋጅ ምንነትና ሌሎች መመሪያዎች ላይ የሚያተኩር ነው።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩብ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኮሎኔል ሸጋው ሙሉጌታ ሲሆኑ የመንግስት ግዥና ንብረት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ለሚያደርጉላቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግነው ስልጠናው በግዥ ሂደት የሚስጠዋሉ ችግሮችን የምንቀርፍበትና በጊዜ፣ በገንዝብ፣ በጥራትና በተወዳዳሪነት ውጤታማ የምንሆንበት በመሆኑ ሁሉም በንቃት መከታተል እንደሚኖርበት አሳስበዋል።
ስልጠናው ዛሬ በኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ ስርዓት ምንነት፣ አተገባበር እና ፋይዳ ላይ ሲያተኩር ስልጠናውን የሰጡት የመንግስት ግዥና ንብረት ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ናቸው።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ በስልጠናቸው የኤሌከትሮኒክ የመንግስት ግዥ (e-GP) አፈጻጸማና ሂደትን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዓላማን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዋና ዋና ተጠቃሚዎችን፣ ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ የተከናወኑ አበይት ተግባራትን፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ አሁን ያለበትን ደረጃ፣ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ያስገኘውን ውጤትና የነበሩ ተግዳሮቶችን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በስልጠናው ውድድርና እኩል እድል መስጠት፣ ገንዘብ የሚያስገኘውን ዋጋ ማስገኘቱ፣ የመንግስትን ህግ ማክበር፣ ወጪን መቀነስ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ዓላማዎች ተብለው የተጠቀሱ ሲሆን ለውጥን ለመቀበል መዘግየት የመሳሰሉት በተግዳሮትነት የቀረቡ ጉዳዮች ናቸው።
በሌላ በኩል መመሪያዎችን ማዘጋጀት፣ አዋጅን ማሻሻል፣ የጥሪ ማዕከል ማደራጀት፣ የሲስተም ልማት፣ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የሲስተም ትስስር መፍጠር ስርዓቱን ለመገንባት ከተከናወኑ ተግባራት ጥቂቶች መሆናቸውን ክብርት ወ/ሮ መሰረት በገለጻቸው አካትተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የኤሌከትሮኒክ ግዥ ያስገኘውን ጥቅም በሚመለከት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥናት ያካሄደ መሆኑን አንስተው በጥናቱም ስራ ያቀላጠፈ መሆኑን፣ ጊዜ ቆጣቢ መሆኑን፣ የህግ ተፈጻሚነት እንዲረጋገጥ ያስቻለ መሆኑን፣ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን መሆኑን፣ ውጪን የሚቀንስ መሆኑን፣ የሰነድ ማጭበርበርን ማስቀረቱን በጥናቱ መረጋገጡን አብራርተዋል።
በመጨረሻም ከሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ስልጠናው ነገም የሚቀጥል ይሆናል።










0 Comments