የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የመጀመሪያ የሆነውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ማረጋገጥ የሚያስችል ስልጠና ከተለያዩ መ/ቤቶች ለተውጣጡ ሰራተኞች በግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ያለዉን የአቅም ክፍተት ለመሙላት የአሰልጣኞች ስልጠና ከህዳር 6 — 24 ቀን 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰጠ፡፡
የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ አበበ በመዝጊያው ንግግር ላይ እንደተናገሩት በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሰርተፊኬት ደረጃ የተሰጠውን ስልጠና ለተከታተሉት ዕጩ አሰልጣኞች በራሳቸው እና በኤጀንሲው ስም ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ አገራችን በዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮ የተቃኘና ከአገራችን ልዩ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ ተዘጋጅቶ በሕግ አውጭው አካል የጸደቀ ዘመናዊ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር የሕግ ማዕቀፍ ያላት ሲሆን፤ይህን የሕግ ማዕቀፍ በትክክል በሥራ ላይ በማዋል ለሃገራችን የኢኮኖሚ እና የመልካም አስተዳደር ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአገር ደረጃ የሚታየውን በተለይ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚታየዉን የአቅም ክፍተት ለመሙላት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding)ተፈራርሞ ዩኒቨርሲቲው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን በመመደብ ሰነዶችን በመገምገም፣ በአሰልጣኝነት የሚመረጡ ባለሙያዎችን መምረጫ መስፈርት በማዘጋጀት፣ከአማካሪ ድርጅቱ የመስሪያ ቢሮዎችን በማመቻቸት እና ሌሎች ስራዎችን በጋራ ሲያከናውን ቆይaል፣ ይህንን በመንግስት እና በልማት አጋሮቻችን ትኩረት የተሰጠውን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና እውን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ወጥቶ ክራውን ኤጀንት የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ የጨረታ ውድድሩን አሸንፎ ለ(Basic, Essential and Advanced levels) የሚያገለግል ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ለሰልጣኞችና ለአሰልጣኞች የሚሆን የስልጠና ሰነድ ተዘጋጅቶ አሁን የደረሰበት የአሰልጣኞች ስልጠና ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የስልጠናና የምክር አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ደበበ በበኩላቸው በግዥና በንብረት አስተዳደር ዙሪያ ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሰርተፊኬት ደረጃ ስልጠና መስጠት በሀገራችን የመጀመሪያና በሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ መሆኑ ደግሞ ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀው ሠልጣኞች ከስልጠናው የገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡
ሰልጣኞችም በቆይታቸው ከስልጠናው ብዙ ዕዉቀት እንዳገኙ ገልጸው፤ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተነስተው ለጥያቄዎቹ በኤጀንሲዉ አመራር ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ለ3 ሳምንታት በቆየው የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር የባለሙያዎች የአሠልጣኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስልጠና ላይ ከተለያዩ መ/ቤቶች የተዉጣጡ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡