በፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ከንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና ከክልልና ተቆጣጣሪ አካላት ጋር 7ኛው ዙር ቋሚ የጋራ የምክክር መድረክ ጉባዔ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ ተካሄደ፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጊዜያዊ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በአገራችን የተዘረጋውን የነጻ ገበያ ስርዓት ኢኮኖሚው ከግብርናው መር ወደ ኢንዱሰትሪ መር እንዲራመድ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ ከጥቃቅንና አነስተኛ እሰከ ከፍተኛ እንዱስትሪዎች እንደአሸን እንዲፈሉ መደረጉንና ከትናንሽ እስከ ሜጋ የመሰረተ ልማቶችንና ፕሮጀክቶችን ነድፎ ተግባራዊ መሆኑንና ከታላቁ የህዳሴ ግድብ እስከ ባቡርና ሰፋፊ ጎዳናዎች ድረስ የሚደረገው እንቅስቃሴ በእውነትም ከድህነት ጋር የገጠምነውን ጦርነት በአሸናፊነት እየተወጣን መሆኑን፣ መንግስትም ለሚያንቀሳቅሳቸው ዘርፈ ብዙ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ማስፈጸሚያ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የሚያገኘው ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የንግዱ ማህብረሰብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ ላይ የተለያዩ ሃላፊዎች ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ የአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደትን በሚመለከት ስለ ተሳታፊ ባለድርሻ አካላት፣ ሰለ አቤቱታ ማጣራት፣ አቤቱታ ሰለማይቀርብባቸውና አቤቱታ ሰለሚቀርብባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣ ስለ አቤቱታ አቀራረብ ሥነ-ሥርዓት፣ በግዥ ፈጻሚው መ/ቤት የሚካሄድ የአቤቱታ ማጣራት ሂደት፣ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ በቦርድ ስለሚከናወን የአቤቱታ ማጣራት ሂደት ያጋጠሙ ችግሮቸና መፍትሄዎቻቸው በፌዴራል መንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በመንግስት ግዥ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች በግሉ ዘርፍ እይታን የመንግስት ግዥ ለምን ትኩረት አስፈለገው? በግዥ አዋጅና መመሪያው የመጡ በጎ ጎኖችና ለውጦች፣ ግልፅነትና ተዓማኒነት ከማስፈንና ፍትሐዊ ተሳትፎን ከማረጋገጥ አንፃር የተካተቱ ለውጦች፣ በግዥ ዙሪያ በአጠቃላይ የሚታዩ ችግሮች፣ በጥናት የተለዩ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸውን በሚመለከት በኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ገለጻ ተደርጓል፡፡
በግዥና ውል አስተዳደር ሰለተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን የመንግስት ግዥና ንብረት ማሰወገድ አገልግሎት ሰለፈጸማቸዉ ግዥዎች፤ በውል አስተዳደር በኩል የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት፣ ሰላጋጠሙ ችግሮች፣ ሰለተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ስለቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን በሚመለከት ከመንግስት ግዥና ንብረት ማሰወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በዝርዝር ቀርቧል፡፡
በወይይቱ ላይ ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፤ ለተነሱ ጥያቄዎችም መልስ ተሰጥል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው የምክክር መድረክ ውይይት ላይ የክልል ተቆጣጣሪ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት