የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች የ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና በቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት በመስጠት መከናወን የሚገባቸው ስትራቴጂያዊ ግብ ተኮር ተግባራትን በተመለከተ የካቲት 10 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዓላማ ባለፈው የ2008 በጀት ዓመት የመጀመሪያው 6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ምን ይመስላል? በቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት በመስጠት መከናወን የሚገባቸው ተግባራትን በተመለከተ የጋራ መግባባትን ለማምጣት መሆኑን ለስብሰባው ታዳሚዎች ገልጸው፣ የውይይቱም ተሳታፊዎች ጥያቄ በመጠየቅና አስተያየት በመስጠት በንቃት መከታተልና መሳተፍ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
አቶ መሥፍን መኮንን የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር ኤጀንሲው የመንግስት ገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ ማስገኘት እንዲያስችል እና በዘርፉ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ ግልፅ፣ ፍትሀዊና በውድድር ላይ የተመሰረተ የመንግስት ግዥ አፈጻጸምን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዲሁም የመንግስት ንብረት አስተዳደር ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ አሰራሮችን ከሪፎርምና ከመልካም አስተዳደር ተግባራት ጋር በማስተሳሰር ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ኤጀንሲው በ2008 በጀት ዓመት ለማከናወን ያቀዳቸው ስትራቴጂያዊ ግብ ተኮር ተግባራት በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ከፍሎ መመልከት እንደሚቻል እነሱም የሪፎርምና የመልካም አስተዳደር ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በሀገራችን እየተመዘገበ ለሚገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፆኦ ማበርከት የሚያስችሉ እና በአዋጅ 649/2001 የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች የሚያሳኩ የሚያስችሉ ግብ ተኮር ተግባራትን ማከናወን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የ2008 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ስድስት ወራት የመደበኛ ሥራዎች አፈፃፀም በአራቱ ዕይታዎች ከተገልጋይ፣ ከፋይናንስ፣ ከውስጥ አሠራር፣ ከመማማርና ዕድገት እይታዎች አንጻር በየዳይሬክቶሬቱ የ2008 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸምን በሚመለከት እንዲሁም ሰለአጋጠሙ ችግሮችና ስለተወሰዱ የማስተካከያ አሰራሮች ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎ የጋራ ግንዛቤ ተወስዷል ፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የኤጀንሲው የ2ዐዐ8 የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ውይይት ላይ ከ80 በላይ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት