የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመተባበር በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር ላይ ጥቅምት 3 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡ወ/ሮ መስከረም ግርማ በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ሚኒስቴር የጤና ባለሙያ የሆኑት ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ ስለ ጡት ካንሰር ምንነት፣ መንስኤዎች፣ ምልክቶች፣ለጡት በሽታ ሊያጋልጡ ስለሚችሉ ልማዶች፣ ሊደረጉ ስለሚገቡ ጥንቃቄዎች፣ የራስን ጡት ስለመመርመር ዘዴ፣ ስለጡት ካንሰር ማረጋገጫ ምርመራዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡አሰልጣኟ በዓለማችን በጡት ካንሰር በሽታ በዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ሰዎች የሚጠቁ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ወደ 75 በመቶ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸውንና በካንሰር በሽታ ምክንያት ለሞት ከተዳረጉ ሰዎች 64.9 በመቶ የሚሆኑት በታደጊ አገሮች የሚገኙ መሆናቸውን የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም አሰልጣኟ ስለማህጸን ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ መንሰኤዎች፣ ምልክቶችና የማህፀን ካንሰርን ለመከላከል ስለሚደረጉ ጥንቃቄዎች ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ ያመጣሉ ተብለው የሚታመኑ ህዋሶችና ድርጊቶች፣ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ፣ ሲጋራ ማጬስ እና ሌሎች ምክንያቶች የሚጠቀሱ መሆኑን ገልጸው፣ሲጋራ አጫሽነትም በዚሁ በሽታ የመጠቃት እድልን ከፍ እንደሚያደርግ እና የማህፀን ጫፍ ነቀርሳ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ሊከሰት የሚችል በሽታ ሲሆን በአብዛኛው በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ሴቶች ለዚህ በሽታ እንደሚጋለጡ አስረድተዋል፡፡በመጨረሻም አሰልጣኟ ከተሳታፊዎች ለተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሰጡና አሰተያየትም የተቀበሉ ሲሆን ሰልጣኞችም ከስልጠናው ጥሩ ገንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው በማህጸን ጫፍ ካንሰርና በጡት ካንሰር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ የሁለቱም መ/ቤት ሴት ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት