The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን አከበረ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብ ሚኒስቴርና የገንዘብ ሚኒስቴር ተጠሪ ከሆኑት ተቋማት ጋር በመሆን በዓለም ለ110ኛ ጊዜ በኢትየጵያ ደግሞ ለ45ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የሴቶች ቀን "መብት የሚያስከብር ማህበረሰብ እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ  በድምቀት አከበረ፡፡

ክብርት ያስሚን ወሃብረቢ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመክፈቻው ንግግር ላይ እንደተናገሩት ሴቶች በሀገራችን ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ እንዳለ  ገልጸው፣ በተለይ ባለፉት ሶሰት የለውጥ ዓመታት ሴቶች በሃገሪቱ ወሳኝ በሆነ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎአቸው በእጅጉ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም ክብርት ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርች 8 የሴቶችን የትግል ታሪክ፣ ሴቶች በቆራጥነት ያገኙትን ድል የምናሰታውስበትና የመጪው ዘመን ትግል በይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚደረግበት ዕለት መሆኑን አሰረድተዋል፡፡በዚህ የሴቶች ክብረ በዓል ላይ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን እና አካል ጉዳተኞችን አስመልክቶ ለተሳታፊዎች የግንዘቤ ማስጨበጫ በባለሙያዎች ተሰጥቷል፡፡ በመጨረሻ ይህንን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት የእንጦጦ ፓርክ የጉብኘት ፕሮግራም ተካሄዷል፡፡ ለአንድ ቀን በቆየው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ክብረ በዓል ላይ ከተሳታፊዎች አሰያየቶች ተሰጥተዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ 35 ከሚሆኑ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶችና የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ የምክክር መድረክ የካቲት 25/2013ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ አካሄደ፡፡

ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመክፈቻውም ንግግር ላይ እንደተናገሩት የመንግስት ግዥን በዕቅድ ላይ በተመሰረተና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም /Value for Money/ ማስገኘት በሚያስችል መልኩ መፈጸም እንዳለባቸው፣ እንዲሁም በዚህ መልኩ የሚገኝን የመንግስትና ህዝብ ሃብት የሆነውን ንብረቶች በአግባቡ ይዘው ሊያስተዳድሩና አገልግሎት ላይ ሊያውሉ እንደሚገባ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሲያልፍም ለበለጠ ጉዳት ከመዳረጋቸው በፊት፣ በሰውና በአከባቢ ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው አስቀድሞ መንግስት በዘረጋው የአወጋገድ ሥርዓት መሠረት ሊያስወግዱ እንደሚገባ በመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 እና በአፈጻጸም መመሪያዎች ተደንግጎ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በአገራችን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ተጠናቆ ቀጣዩ*ኢትዮጵያ አፍርካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል የሚታወቀው ከ2013ዓ.ም እስከ 2022ዓ.ም የሚቆየው የ10 ዓመት ዕቅድ እና የዚሁ አካል የሆነው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመተግበር ላይ እንደሚገኝ፣ የተጠናቀቀውም ሆነ ወደ ትገበራ በመግባት ላይ የሚገኘው የልማትና የእድገት ዕቅዶች ማዕከል ያደረጉት አረንጓዴ ኢኮኖሚን መሆኑን፣ በዚህም ረገድ በተጠናቀቀው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ወቅት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያግዙ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመሠረተ ልማት ዘርፎች፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፎች መልካም የሚባሉ ጅምሮችና ውጤቶች መመዝገባቸውን እና እነዚህ መልካም ጅምሮች የታዩባቸውን ድክመቶች በማረም ለቀጣዩ ዕቅድ ትግበራ እንደ መንደርደሪያ የሚያለግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከተሳታፊዎች ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ተጠይቀው መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡

በፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የ2013 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን በተመለከተ ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከበላይ ኃላፊዎች፣ ከማኔጅመንት አባላት እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር የ2013 የበጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን በተመለከተ ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

በኤጀንሲው ዳይሬክተሮች በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ዋና ዋና ሥራዎችን፣ የተከናወኑ ሥራዎችን፣ ያጋጠሙ ችግሮችን፣ የመፍትሄ ሃሳቦችን፣ ትኩረት ሊደረግባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮችና ከመደበኛ ሥራ ውጭ ስለተከናወኑ ሥራዎች ከተገልጋይ፣ ከውስጥ አሰራር፣ ከፋይናንስ እና ከመማርና ዕድገት ዕይታዎች አንጻር ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም የኤጀንሲው የበላይ ኃላፊዎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ከተሳታፊዎች የተሰጡ አስተያየቶችን የተቀበሉ ሲሆን፣ ለተጠየቁ ጥያቄዎችም መልስ በመስጠትና ተጨማሪ ሀሳቦችን በማከል ወይይቱን አሳታፊ አንዲሆን አድርገውታል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከሠራተኞች  አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ተነስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው የ2013 የበጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርትን በተመለከተ ውይይት ላይ የበላይ ኃላፊዎች፣ የማኔጅመንት አባላት እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

የኢፌድሪ የመ.ግ.ን.አ.ኤ.የህዝብ ግንኑነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና ተሰጠ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሰበመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ዙሪያ ከተለያዩ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች ለተውጣጡ የግዥ ዳይሬክተሮችና የግዥ አጽዳቂ ኮሚቴ አባላት ከታህሳስ 15-17 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና ሰጠ፡፡

ሥልጠናውን የሰጡት በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክተሮችና የግዥና ንብረት ባለሙያዎች ሲሆኑ፣ ስለመንግስት ግዥ ምንነት? የመንግስት ግዥ ስለሚመራባቸው ህጎች፣ ስለመንግስት ግዥ መርሆዎች፣ ስለ መንግስት ግዥ አፈጻጸም ተግባርና ኃላፊነት፣ ስለግዥ ሥርዓትና ዑደት፣ ስለጨረታ ሰነድ ዝግጅት፣ ስለመንግስት ግዥ እና ስለመንግሥት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በዚህ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥልጠና ላይ ግዥና ንብረትን በሚመለከት ለቀረቡት የመወያያ ጥያቄዎች ሠልጣኞች በቡድን በመወያየት  ምላሽ ሰጥተዋል፡፡በዚህ ሶስት ቀናት በቆየው ሥልጠና ላይ ሠልጣኞች የዕውቀት ሽግግርን አግኝተው በሥራቸው ላይ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ ይታመናል፡፡

የኢፌድሪ የመ.ግ.ን.አ.ኤ.የህዝብ ግንኑነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት



የመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚመራበት የግዥና የንብረት መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተውጣጣ ኮሚቴ በማዋቀር በመንግስት ግዥ አስተዳደር መመሪያ፣ በመንግስት ንብረትና የተሽከርካሪ አጠቃቀም መመሪያ እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በሚመለከት የአምራች ዘርፍ፣ የፋይናንስ ዘርፍ እና የአገልግሎት ዘርፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አጠቃቀም መመሪያ ላይ በተከታታይ አምስት ዙሮች በአዳማ ከተማ የማሻሻያ ስራ እያደረገ ይገኛል፡፡
አቶ ወልደአብ ደምሴ የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ በየነ ገብረመስቀል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እና አቶ ዳዊት ሽመልስ በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግስት ወጪ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በጋራ ሆነው በቦታው በመገኘት ለመመሪያ መሻሻያ ኮሚቴነት ለተሳተፉት ባለሙያዎች የሥራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከተለያዩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች የተውጣጣ በቁጥር 26 ያክል የመመሪያ ማሻሻያ ኮሚቴዎች በግንባታ ግዥ (Procurement Works) እና አለም አቀፍ ግዥን(International Procurement) በሚመለከት በአዲስ አበባ ፍሬንድሺፕ ሆቴል ከመስከረም 2/2013 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ተከታታይ ዙሮች ለመመሪያ መሻሻያ ኮሚቴነት ለተሳተፉት ባለሙያዎች  የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የተሰጣቸው ሲሆን በስልጠናው የተሳተፉ ባለሙያዎች ከስልጠናው ለመመሪያ ማሻሻያው ጥሩ የሆነ ግብዓት እንዳገኙ ከኮሚቴዎቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት