The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

መንግስት ፋይናንስ፣የግዥና የንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ ውይይት ተካሄደ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመንግስት ፋይናንስ፣የግዥና የንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አደራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የስብሰባው ዋና ዓላማ የማሻሻያ ሥራ እየተሰራላቸው ባሉት በፌዴራሉ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና በመንግሥት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አዋጅ ዙሪያ የዘርፉ ፈጻሚ ከሆኑት ከፌዴራል መንግስት መስራ ቤቶች የተዉጣጡ ባለሙያዎችና የስራ ኃለፊዎች ጋር በመመካከር የጋራ ግንዛቤን ማሳደግና በህግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ላይ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን ገንቢ ግብአት እንዲሰጡ በመጠየቅ የዉይይት መድረኩን አስጀምረዋል፡፡
በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና ግዥ አፈጻጸም ውስጥ ሊከሰት የሚችል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን በአገር ደረጃ ከምንጩ ለማድረቅ እና ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሠራርን እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ ከፈጻሚ የመንግስት አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠበቅ ኣክለዉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ታደሰ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የፌዴራል መንግስት የፋይናንስ ማሻሻያ ረቂቅ ሕጎችን ዋና ዋና ነጥቦችን በማንሳት ስለማሻሻያው ዓብይ ምክንያቶች፣ስለተሻሻሉ ዋና ዋና ድንጋጌዎች፣ከፕሮገራም በጀት አንጻር ስለተሻሻሉ ድንጋጌዎች አና በአፈጻጸም ስለአጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጆንሴ ገደፋ በበኩላቸዉ በአዲሱ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ረቂቅ ውስጥ ስለተካተቱ ዋና ዋና ለውጦች እና ከግዥ የገንዘብ ጣሪያ እና ከግንባታ ሥራ አፈጻጸም መመሪያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች፣ ሰለዓለም ዓቀፍ ግልጽ ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ፣በግንባታ ሥፍራ ላይ ከሚገኙ ማቴሪያሎች ክፍያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ገለጻ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለአንድ ቀን በቆየው የመንግስት ፋይናንስ፣የግዥና የንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆች ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከተለያዩ ፌዴራል መስራ ቤቶች የተዉጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

በመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የፌዴራል የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዙሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም በአሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሄደ፡፡
የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዋና ዓላማ የማሻሻያ ስራ እየተሰራ ባለው በፌደራሉ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ዙሪያ የዘርፉ ባለድርሻ ከሆነው የንግዱ ህብረተሰብ አባላት ጋር በመመካከር የጋራ ግንዛቤን ማሳደግና በህግ ማዕቀፉ ማሻሻያ ላይ የንግዱ ህብረተሰብ አባላት የበኩላቸውን ግብዓት እንዲሰጡ በማሰብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የተዘረጋውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት በትክክል ተግባራዊ በማድረግ ተገልጋዮችን ማርካት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባለፈ የመልካም አስተዳደር መገለጫ አንዱና ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ገልፀው የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በንቃት እንዲከታተሉና እንዲሳተፉ በማሳሰብ  መድረኩን  በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በመቀጠልም በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ግዥ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነቢዩ ኮከብ በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ የተካተቱ ዋና ዋና ለውጦችና ከግዥ የገንዘብ ጣሪያ እና ከግንባታ ስራ የአፈፃፀም መመሪያ ጋር በተያያዘ አዲስ በተጨመሩና በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ በዝርዝር ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡ 
አቶ ነጋሽ ቦንኬ የመንግሥት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር በበኩላቸው የፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር የሚመራባቸው የህግ ሰነዶች በፌደራል መንግስት የግዥ ሂደት አቅራቢዎች በመንግስት መ/ቤቶች ላይ የሚቀርብ አቤቱታ እና መንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ የሚቀርብ የጥፋተኝነት ሪፖርት፣በተጫራቾች የሚቀርቡ የአቤቱታ መነሻዎች፣የአቤቱታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት፣ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪ ውሳኔ ሰጪ ቦርድ አባላትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ አወያይነት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች፣አስተያየቶችና ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎችና ሃሳቦች በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የበላይ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር  አቶ ፀጋዬ አበበ በተሳታፊዎች የተሰጠው አስተያየት ገንቢ እንደሆነና የተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቀረ የሚባል አስተያየት፣ ጥያቄና ሃሳብ ካለ ተሳታፊዎች በፅሁፍ፣ በግንባርና በኢሜይል ለኤጀንሲው በማቅረብ ግብዓቶቹን መጠቀም እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

ኤጀንሲው ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጀ


የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በመልካም አሰተዳደር ንቃናቄ ዙሪያ ጥር 20 ቀን 2008ዓ.ም. በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ውይይት አደረገ፡፡
የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጆንሴ ገደፋ እንደተናገሩት የስብሰባው ዋና አጀንዳ በመንግስት የግዥ እና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ላይ ሊደረጉ የታሰቡ ማሻሻያዎችን እና ተሻሽለው ሥራ ላይ የዋለው በተለይም የግንባታ ዘርፍ ማነቆዎች ተብለው የተለዩ ጉዳዮች፣ከመንግስት የግዥ አፈጻጸም ዙሪያ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋሞች መብትና ግዴታዎች፣በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ የሚቀርቡ አቤቱታዎች እና የውሳኔ ሃሳቦች እንዲሁም በመንግስት የግዥ አፈጻጸም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የሚያጋጥሙያቸዉ የገበያ ትስስር ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም በዚህ መድረክ የተገኙት አካላት በአጀንዳዎቹ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ለማሻሻያው ጠቃሚ የሆኑ ግብአቶችን በመስጠትና ለወደፊቱም በተመሳሳይ መልኩ የተለያዩ መደረኮችን በጋራ በማዘጋጀት ውይይቱ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልጸው ውይይቱን በይፋ ከፍተዋል፡፡
አቶ ነብዩ ኮከብ በፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ውስጥ ስለተካተቱ ዋና ዋና ለውጦች እና ከግዥ የገንዘብ ጣሪያ እና ከግንባታ ሥራ አፈጻጸም መመሪያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች፣ ሰለዓለም ዓቀፍ ግልጽ ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ፣ በግንባታ ሥፍራ ላይ ከሚገኙ ማቴሪያሎች ክፍያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
አቶ ትግስት ደበበ በፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር በፌዴራል መንግስት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መብትና ግዴታዎች፣በአቅራቢዎች በኩል ሰለሚታዩ ግድፈቶች፣በፌዴራል መንግስት ግዥ ዙሪያ በአቅራቢዎች በመንግስት መ/ቤቶች ላይ ሰለሚቀርቡ አቤቱታዎች እና በመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ ስለሚቀርቡ የጥፋተኝነት ሪፖርቶችን በመዘርዘር አሰረድተዋል፡፡
አቶ ዘሪሁን አለማየሁ በፌደራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው በመንግስት የግዢ አፈፃፀም ዙሪያ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ያጋጠማቸው ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀረበው ገለጻ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለአንድ ቀን በቆየው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር የተካሄደ የህዝብ ክንፍ የውይይት መድረክ ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የመጡ ተሳታፊዎች እና የተለያዩ መ/ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የግንባታ ስራን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ላይ ውይይት ተደረገ

የአፈፃፀም መመሪያውም ከጥር 01 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በሚሻሻለው የግንባታ ስራ ረቂቅ የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ላይ ታህሳስ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡
የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ የውይይቱን ሪቂቅ ሰነድ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ዓላማው በአዋጅ ቁጥር 649/2001 ዓ.ም በግዥ ዙሪያ አላሰራ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቅራቢው በግንባታ ሥራ የግዥ የብቃት መስፈርት አወሳሰንና ትርጓሜን፣አጠቃላይና ተዛማጅ የሥራ ልምድን፣የፋይናስ አቋምን፣ዓመታዊ የተርን ኦቨር መጠንን፣በግንባታ ሥራ ላይ የሚሰማሩ ባለሙያዎች የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን፣ የግንባታ ሥራ መሟላትን በተመለከተ ሠፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ከአንድ በላይ ንዑሳን የግንባታ ሥራዎች (lots) በተካተቱበት ግዥ ላይ የልምድ አያያዝን፣ለህንፃ ግንባታ ሥራ የሚጠየቅ ዝቅተኛ መስፈርት፣ለድልድይ ግንባታ ሥራ የሚጠየቅ ዝቅተኛ የግንባታ መስፈርት፣የመንገድ ፕሮጀክቶች አመዳደብ በንጣፍ ዓይነት፣ለመንገድ ፕሮጅቶች የግንባታ ሥራ የሚጠየቅ ዝቅተኛ መስፈርት፣እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡
አቶ ጆንሴ የመመሪያው አንቀፅ 22(1) መንደርደሪያ ተሰርዞ የመንግስት መ/ቤት የምክር አገልግሎት የግዥው ግመታዊ ዋጋ ከብር 900,000 (ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር)የሚበልጥ በሚሆንበት ጊዜ በምክር አገልግሎቱ አቅርቦት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ ጥሪ ማድረግ ይኖርበታል በሚለው ሀሳብ መካተቱን ገልፀዋል፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር በክቡር አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ እና በሚንስትር ዴኤታው በክቡር  አቶ አለማየሁ ጉጆ አወያይነት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና  አስተያየቶች  የተነሱ ሲሆን ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የግዥ አፈፃፀም  መመሪያውም ከጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲና የባለድርሻ አካላት  የግንባታ ስራን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ውይይት ላይ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡                   

የሙያ ብቃትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ሥልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የመጀመሪያ የሆነውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ማረጋገጥ የሚያስችል ስልጠና ከተለያዩ መ/ቤቶች ለተውጣጡ ሰራተኞች በግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ ያለዉን የአቅም ክፍተት ለመሙላት የአሰልጣኞች ስልጠና  ከህዳር 6 — 24 ቀን 2008 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ሰጠ፡፡
የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጸጋዬ አበበ በመዝጊያው ንግግር ላይ እንደተናገሩት በአገራችን የመጀመሪያ የሆነውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሰርተፊኬት ደረጃ የተሰጠውን ስልጠና ለተከታተሉት ዕጩ አሰልጣኞች በራሳቸው እና በኤጀንሲው ስም ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ አገራችን በዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮ የተቃኘና ከአገራችን ልዩ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ ተዘጋጅቶ በሕግ አውጭው አካል የጸደቀ ዘመናዊ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር የሕግ ማዕቀፍ ያላት ሲሆን፤ይህን የሕግ ማዕቀፍ በትክክል በሥራ ላይ በማዋል ለሃገራችን የኢኮኖሚ እና የመልካም አስተዳደር ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአገር ደረጃ የሚታየውን በተለይ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚታየዉን የአቅም ክፍተት ለመሙላት ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ ለመስራት  የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ (Memorandum of understanding)ተፈራርሞ ዩኒቨርሲቲው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላትን በመመደብ ሰነዶችን በመገምገም፣ በአሰልጣኝነት የሚመረጡ ባለሙያዎችን መምረጫ መስፈርት በማዘጋጀት፣ከአማካሪ ድርጅቱ የመስሪያ ቢሮዎችን በማመቻቸት እና ሌሎች ስራዎችን በጋራ ሲያከናውን ቆይaል፣ ይህንን በመንግስት እና በልማት አጋሮቻችን ትኩረት የተሰጠውን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ሥልጠና እውን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ግልጽ ጨረታ ወጥቶ ክራውን ኤጀንት የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ የጨረታ ውድድሩን አሸንፎ ለ(Basic, Essential and Advanced levels) የሚያገለግል ሥርዓተ ትምህርት ተቀርጾ ለሰልጣኞችና ለአሰልጣኞች የሚሆን የስልጠና ሰነድ ተዘጋጅቶ አሁን የደረሰበት የአሰልጣኞች ስልጠና ማከናወን መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የስልጠናና የምክር አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ደበበ በበኩላቸው በግዥና በንብረት አስተዳደር ዙሪያ ባለሙያዎችን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ ተቋማዊ በሆነ መንገድ በሰርተፊኬት ደረጃ ስልጠና መስጠት በሀገራችን የመጀመሪያና በሲቪል ሰርቪስ ዩንቨርሲቲ መሆኑ ደግሞ ልዩ እንደሚያደርገው ገልፀው ሠልጣኞች ከስልጠናው የገኙትን ዕውቀት በመጠቀም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል፡
ሰልጣኞችም በቆይታቸው ከስልጠናው ብዙ ዕዉቀት እንዳገኙ ገልጸው፤ የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶችም ተነስተው ለጥያቄዎቹ በኤጀንሲዉ አመራር ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ለ3 ሳምንታት በቆየው የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር የባለሙያዎች የአሠልጣኞች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ስልጠና ላይ ከተለያዩ መ/ቤቶች የተዉጣጡ  ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡