The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

News

የ2010 በጀት ዓመት የ6 ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በሚመለከት ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች የ2010 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በተመለከተ ጥር 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ተ/ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዋና ዓላማ የ2010 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸማችን ምን እንደሚመስልና በቀጣይ የስድስት ወራት በጀት ዓመት ለምንሰራው ስራ አቅጣጫ መያዝ እንዳለብን፣ አዲስ በተዘጋጀው የውጤት ተኮር መመሪያ እና የምደባ አካሄድ እንዲሁም በሙሰና መከላከል ሰትራቴጂክ ዕቅድ ላይ በማተኮር ውይይት እንደሚደረግ በመግለጽ ስብሰባውን ከፍተዋል፡፡

አቶ አድማሱ ማሞ የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የ2010 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን በሚመለከት የለውጥና የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የመደበኛ ሥራዎች የ2010 የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም በጥንካሬና በዕጥረት የታየ ሲሆን፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዕቅድ አፈፃፀምን በማጠቃለል፣ በከይዘን፣ በለውጥና መልካም አስተዳደር ዙሪያ ባጋጠሙ ችግሮችና በተወሰዱ የማስተካከያ አሰራሮች ላይ በሰፊው ውይይት አድርገዋል፡፡አቶ መስፍን መኮንን የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በተሻሻለው የውጤት ተኮር ዕቅድ ዝግጅት፣ ትግበራና የአፈጻጸም ምዘና መመሪያ መነሻዎች፣ ዓላማዎች፣ የሰራተኛ የውጤት ተኮር ዕቅድ ዝግጅት፣ የአፈፃፀም ስምምነት፣  ክትትልና  ግምገማ፣ የአፈጻጸም ምዘና፣ የውጤት ተኮር ሥራ አፈጻጸም ምዘና ደረጃ አሰጣጥ፣ድህረ ምዘና ተግባራት እና የልዩ ልዩ አካላት ተግባርና ኃላፊነትን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ መስፍን በነጥብ የሥራ  ምዘናና  ደረጃ  አወሳሰን  የድልድል  አፈፃፀም  መመሪያን በሚመለከት ስለድልድል መመሪያው ዓላማ፣ መርሆዎች፣ የሠራተኛ ውድድር/ድልድል አፈጻጸም፣ አዎንታዊ ድጋፍ፣ የሠራተኞች ለድልድል ማሟላት  የሚገባቸው  ቅድመ ሁኔታዎች፣ የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሂደት እና የመመዘኛ መስፈርቶች ላይ ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

የተቆጣጣሪነት ሚና ካላቸው መ/ቤቶች ለተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ዋና ኦዲተር እና የፍትህ አካላት በመንግሥት ግዥ  አፈጻጸም ዙሪያ ከታህሳስ 24—26 ቀን 2010 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒሰቴር የስብሰባ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡ አቶ ታደሰ ከበደ በመንግሥት ግዥ አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን ስለመንግሥት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ ዓላማና መርሆዎች፣ የመንግሥት ግዥ ሰለሚመራባቸው የህግ ማዕቀፎች፣ ሰለመንግስት ግዥ ትርጓሜ፣ ሰለመንግስት ግዥ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ልዩ ባህሪያትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች፣ ስለመንግስት ግዥ ዓይነቶችና ሂደት እንዲሁም የመንግሰት ግዥ ስለሚመራባቸው ሕጋዊ ሠነዶች በዝርዝር ገላጻ አድርገዋል፡፡

አቶ ገበያው ይታይህ በመንግሥት ግዥ አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ከግዥ ዕቅድ በመነሳት ሰለግዥ ዕቅድ አሰፈላጊነትና ጥቅም፣ ሰለ ግዥ ዑደትና የግዥ ዘዴዎች ስለሆኑት ገልጽ ጨረታ፣የመወዳደሪያ ሃሰብ መጠየቂያ፣ የሁለት ደረጃ ጨረታ፣ ውስን ጨረታ፣ ዋጋ ማቅረቢያ፣ አንድ አቅራቢ እና በማዕቀፍ ስምምነት ስለሚፈጸም ግዥ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ እፀገነት ቢሻው በግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ሰለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት አጠቃላይ ገጽታ፣ ሥነ—ሥርዓቱ ሰለሚመራባቸው ህጎች፣ ሰለተሳታፊ ባለድርሻ አካላት፣ ሰለአቤቱታ ማጣራት እና ስለ ጥፋተኝነት ሪፖርት  ትርጉም፣ በአፈጻጸም ወቅት ስለምያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው እንዲሁም በመ/ቤቶችና በአቅራቢዎቸ ስለሚታዩ ግድፈቶች ሰፋ ያለ መብራሪያ ሰጥተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለሶስት ቀን በቆየው የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው  አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ 60 የሚሆኑ የየመ/ቤቶቹ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት


በሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፎረም አደረጃጀትን በተመለከተ ሥልጠና ተሰጠ አዋጅ ቁጥር 1064/2010 የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ  ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በመተባበር በሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፎረም አደረጃጀትን በተመለከተ ታህሳስ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
አቶ ብርሃኑ ታደለ በፐብሊክ ሰርቪስ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ስለሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ሊሻሻል ሰለተፈለገበት ምክንያቶች በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚካሄደውን የምልመላና መረጣ ሥርዓትን በመሰረታዊነት በመለወጥና በአገር አቀፍ ደረጃ የሙያና የሥራ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት በመዘርጋት፣ እንዲሁም የመንግስት ሠራተኛው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ብዝሀነትን ያረጋገጠና ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለችውን እድገት ለማስቀጠል የሚያስችል ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባትና የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም በሰው ሃብት ሥራ አመራር ረገድ ያመጣቸውን ውጤቶች ለማጎልበትና ለማስቀጠል የሚያስችል ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም አሰልጣኙ አዋጁ 12 ክፍሎች ያሉት ሲሆን በክፍል ሶስት አንቀጽ 19፣ በክፍል አራት ንኡስ ክፍል ሁለት አንቀጽ 42 እና በክፍል አምስት አንቀጽ 48 ላይ ለሴት ሠራተኞች ልዩ ትኩረት በመስጠት የተለያዩ ድንጋጌዎች መካተታቸውን፣ አንቀጽ 19/5 በሙከራ ላይ ያለ የመንግሥት ሠራተኛ በሥራ ምክንያት በሚመጣ በሽታ ወይም በሥራ ላይ በሚደርስ አደጋ ምክንያት ከሥራ የቀረ እንደሆነ ያልጨረሰውን የሙከራ ጊዜ ከሕመሙ ወይም ከጉዳቱ ከዳነበት ጊዜ አንስቶ እንዲጨርስ እንደሚደረግ፣ አንቀጽ 19/7 የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) ድንጋጌ ቢኖርም በወሊድ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ በሥራዋ ላይ ያልተገኘች የሙከራ ሠራተኛ የወሊድ ፈቃዷ እንደተጠናቀቀ የሙከራ ጊዜ እንድትጨርስ እንደሚደረግ፤ ሆኖም በሙከራ ሥራዋ ላይ ያልተገኘችበት ጊዜ ከአንድ ወር በታች ከሆነ የሥራ አፈጻጸም ምዘና ውጤቷ በሥራ ላይ በቆየችበት ጊዜ ታስቦ እንደሚሞላላት፣ የወሊድ ፈቃድንም በሚመለከት ነፍሰጡር የሆነች የመንግሥት ሠራተኛ መውለጃዋ ሲደርስ እወልዳለሁ ብላ ከገመተችበት ቀን በፊት 30 ተከታታይ ቀናት የቅድመ ወሊድ ፈቃድ፣ እንዲሁም ስትወልድ ከወለደችበት ቀን ጀምሮ 90 ተከታታይ ቀናት፣ በአጠቃላይ 120 ተከታታይ ቀናት ደመወዝ የሚከፈልበት የወሊድ ፈቃድ እንደሚሰጣት፣  ሴቶች በቅጥር፣ በደረጃ እድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡ወ/ሮ ሊዲያ ንጋቱ በፐብሊክ ሰርቪስ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት የስርዓተ ፆታ ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት የፎረም አደረጃጀትን በተመለከተ ፎረም ማለት ምን ማለት ነው? ለሴቶች በመ/ቤት /ፎረም መመስረት/ የሚኖረው ፋይዳ፣ በፌዴራል ተቋማት የሴቶች ሠራተኞች ፎረም ለማቋቋም ዝርዝር ዓላማ፣ በፌዴራል መንግስት ተቋማት የፎረም አስፈላጊነት፣ የፌዴራል መንግስት ተቋማት ፎረም አመሠራረት፣ የሴት ሠራተኞች ፎረም መተዳደሪያ ደንቡ ሲዘጋጅ በውስጡ የሚኖረው ይዘት የሚለውን በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹም ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለግማሽ ቀን የቆየው በሲቪል ሰርቪስ መመሪያዎች፣ ህጎች እና የፎረም አደረጃጀት በተመለከተ ሥልጠና ላይ የሁለቱም መ/ቤት ሃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡


የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በሰብዓዊ መብት ዙሪያ ለኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ

በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለመላው የኤጀንሲው ሠራተኞች በሰብዓዊ መብት ዙሪያ በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ ታህሳስ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ፡፡ ወ/ሮ መሠረት ማሞ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ በሥልጠናውም ከሰብዓዊ መብቶች መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ተነስተው ስለመብቶቹ ትርጉም፡- እነዚህ መብቶች መሰረታቸው የሰው ልጅ ክብርና ዋጋ ነው ለማለት የሚቻል ሲሆን የእነዚህ መብቶች ምንጭ የሰው ልጅ ተፈጥሮ መሆኑንና ሰብዓዊ መብቶች በተፈጥሮ ያገኘናቸው መብቶችና ነጻነቶች ናቸው ቢባሉም ሕግ በበኩሉ እነዚህ መብቶች እንዲከበሩ፣ እንዲተገበሩ እውቅ እና ጥበቃ እንዲያገኙ ለማስቻል ከፍተኛ ሚና እንዳለው አሰረድተዋል፡፡

በመቀጠልም አሰልጣኟ የሰብዓዊ መብቶች ታሪካዊ አመጣጥ፣ የሰብዓዊ መብቶች ባህሪያትና አመዳደብ፣ የሰብዓዊ መብቶች ገደቦች እና እገዳዎች፣ ሰብዓዊ መብቶችና የመንግስት ግዴታዎች፣የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ማስፈፀሚያና መከታተያ ሥርዓትና ሕጎች፣ አለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ይዘት የሰብዓዊ መብት እና የመልካም አሰተዳደር ትስስር/ቁርኝትን በሚመለከት ሰፋ ያለ ገለጻ አድርገዋል፡፡አቶ ታደሰ ተሰማ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሰብአዊ መብት ግንዛቤ ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ሰለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ሰብአዊ መብቶችን ያማከለ አሰራር ለልማት ማለት በየትኛውም የልማት ስራ ሂደት ውስጥ የአለም አቀፍ እና ሃገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን ማስከበር እና ማክበር በሚያስችል መንገድ አጣምሮ ማስኬድንየሚያረጋግጥ የአሰራር ስርአት መሆኑን፣ ስለድህነት ትርጉም፣ድህነት ከሰብአዊ መብቶች መረጋገጥ ጋር ቁርኝት እንዳለው፣(ማህበራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ መብቶች ጋር)፣ የሰብአዊ  መብቶች፤ ልማት እና ድህነት ቅነሳ ስላላቸው ግንኙነት በሰፊው ገልጸዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የዕለቱ ሥልጠና ተጠናቋል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

በአቅራቢነት ስለመመዝገብ

በኤጀንሲያችን ድረ-ገጽ ላይ በአቅራቢነት በቀላሉ ለመመዝገብ እንዲችሉ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀውን የአጠቃቀም ማኑዋል (User Guide for Supplier) በቅድሚያ መመልከት እንዳለብዎት አይርሱ፡፡ በመመሪያው መሠረት ምዝገባዎን ያከናውኑ፡፡

More Articles...