The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግሥት ግዥና ንብረት ታሪካዊ አመጣጥ

የመንግሥት ግዥ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ አንድ ጊዜ በተማከለ በሌላ ጊዜ ደግሞ ባልተማከለ መንገድ ሲፈፀም እንደነበር ቀደምት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይኸዉም፡-
ከ1935ዓ.ም እስከ 1950 ዓ.ም የሁሉም መንግሥት መ/ቤቶች ግዥ ተጠቃሎ በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት ይከናወን እንደነበርና አፈፃፀሙ ከፍተኛ መዘግየትና አልፎ አልፎም የአገልግሎት መቋረጥ ይታይበት ስለነበር ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን አሠራር ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉ፡፡
ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት ንብረት ሚ/ር /Ministry of stores and supplies/ የሚባል እራሱን የቻለ መ/ቤት እንዲመሰረት ተደርጎ የመንግሥት መ/ቤቶች ግዥ ተጠቃሎ ይከናወን እንደነበርና የዚህ ሚ/ር መ/ቤት አመሰራረት በቂ ጥናት ያልተደረገበትና በችኮላ የተቋቋመ በመሆኑ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀምን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ችግሩን ስላባባሰው ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ፈርሶ የገንዘብ ሚኒስቴርና የዋናው ኦዲተር መ/ቤት ሁሉም አስፈፃሚ የመንግስት መ/ቤቶች የሚመሩበትን የግዥ መመሪያ በጋራ በማዘጋጀት ከብር 150,000,00 በላይ የሆኑትን የመንግሥት መ/ቤቶች ግዥ አፈፃፀም የሚመረምር ማእከላዊ የግዥ ኮሚቴ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ይሁን አንጂ በዚህም አሠራር የመንግሥት ግዥ ችግሮች ከመወገድ ይልቅ በመባባሳቸው መ/ቤቶች በማዕከላዊው የግዥ ኮሚቴው ቁጥጥር የሚደረግበትን የገንዘብ ጣሪያ ለመሸሽ ሲሉ ግዥዎቻቸውን እየከፋፈሉ በቁጥቁጥ መግዛት ስለጀመሩ አሠራሩ ከታሰበው ዓላማ ውጭ የጥቅል ግዥ በተበታተነ ግዥ እንዲተካና በአስቸኳይነት ሽፋን አብዛኞቹ ግዥዎች የግልፅ ጨረታ ሂደትን ባልተከተለ መንገድ እንዲፈጸሙ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ በመቻሉ፡፡
ለተፈጠረው የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም ችግር መፍትሄ ለመስጠት በ1969 ዓ.ም የመንግሥት ዕቃ ግዥና አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መምሪያ በሚል መጠሪያ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር አንድ የሥራ ክፍል ተዋቅሮ እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ መጠናቸው እስከ ብር 150,000,00 ድረስ ያሉ ግዥዎችን አስፈፃሚ መ/ቤቶች በራሳቸው እንዲፈፅሙ የግዥ ስልጣን (ውክልና) በመሥጠትና ከዚያ በላይ የሆኑ ግዥዎችን ግን ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎች መ/ቤቶች ተውጣጥቶ በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት እየተመረመሩ እንዲፈፀሙ ሲደረግ ቆይቷል፡፡በዚህ አሠራር ችግሮቹ በተወሰነ ደረጃ የተቃለሉ ቢሆንም ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የመንግሥት ግዥ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ የሚመራበት ሁኔታ ተጠንቶ በወጣው የ1973ቱ የፋይናንስ ደንብ ቀደም ሲል ለመንግሥት መ/ቤቶቹ ተሰጥቶ በነበረበት ወቅት የግዥ ስልጣን ውክልና ከብር 150,000,00 ወደ ብር 250,000,00 ከፍ እንዲል ተደጓል፡፡
በ1973 የፋይናንስ ደንብ መሠረት በመንግሥት እቃ ግዥና አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መምሪያ ሥር የማዕከላዊ ጨረታ ውሳኔ መርማሪ ኮሚቴ ጽ/ቤት የሚባል የሥራ ክፍል ተመስርቶ ከብር 250,000,00 በላይ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ግዥዎችን አስቀድሞ የጨረታ ዶክመንቶችን እየመረመረ ግዥውን ሲፈቅድ ከቆየ በኋላ በመቀጠል በ1986 የገንዘብ ሚ/ር መዋቅር በአዲስ መልክ ሲጠና የመንግሥት ዕቃ ግዥና አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መምሪያ እንዲታጠፍ ተደርጎ በጠቅላላው 3 የሰው ሃይል ያለው የግዥ ዩኒት በመባል በምክትል ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሥር ተቋቁሞ እስከ 1991ዓ.ም ድረስ ግዥው የሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች ተወካዮች በአባልነት በሚሳተፉበት የማዕከላዊ ጨረታ ውሳኔ መርማሪ ኮሚቴ አማካኝነት እተገመገመ ተቀባይነት ሲያገኝ ግዥው ሲፈፀም ቆይቷል፡፡
ከመጋቢት 1991ዓ.ም ጀምሮ በመምሪያ ደረጃ ተቋቁሞ የመንግሥት ግዥ መመሪያ ቁጥር 1/1991 ስራ ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን የአስፈፃሚ መ/ቤቶች የግዥ ስልጣን ውክልናም በዚህ መመሪያ መሠረት ሁለት ቦታ ተከፍሎ ለአገር ውስጥ ግዥ እስከ ብር 500,000 ለአለም አቀፍ ግዥ ደግሞ እስከ ብር 2,000,000 ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
በየጊዜው የሚደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ በ1993ዓ.ም የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር መምሪያ በስሩ ሶስት ቡድኖች ማለትም ፡-
1.የጨረታ ምርመራና ግምገማ ቡድን፣
2.የግዥ ጥናትና መረጃ ማደራጃ ቡድን፣
3.የመንግስት ንብረት አስተዳደር ቡድን፣
እንዲኖሩት በማድረግና አዲስ አደረጃጀት በመፍጠር በ1997 ዓ.ም የመንግሥት ግዥ ኤጀንሲ በአዋጅ እስኪቋቋም ድረስ ከላይ በተጠቀሰው አደረጃጀት በመጋቢት ወር 1991ዓ.ም በወጣው የግዥ መመሪያ መሠረት መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ከሞላ ጎደል ሲወጣ ቆይቷል፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር መምሪያ በቀድሞው በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሥር የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ጥናት በግምባር ቀደምትነት እንዲካሄድባቸው ከተመረጡት መምሪያዎች ውስጥ ንብረትን ሳይጨምር ግዥውን በተመለከተ ሥራ እንደመሆኑ መጠን ከ1995ዓ.ም እስከ 1996ዓ.ም ድረስ በመምሪያው ይሰጡ የነበሩትን አገልግሎቶች ችግር በአግባቡ የፈተሸና ለኤጀንሲው መወለድ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ የማሻሻያ ጥናት ለማካሄድ ተችሎዋል፡፡  
በመሆኑም በማሻሻያ ጥናቱ መሠረት በ1997 ዓ.ም የመንግሥት ግዥን ሙሉ ለሙሉ ለግዥ ፈፃሚ አካላት በመስጠትና ወደ አልተማከለ አሠራር በመቀየር ለበርካታ አመታት ሲንከባለሉ ለቆዩት አብዛኞቹ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም ችግሮች መፍትሄ የሰጠና በተበታተነ መልክ ሲሰራባቸው የቆዩትን የግዥ ደንብና መመሪያዎችን በማጠቃለልና በማሻሻል፣የመንግሥት ግዥ አዋጅ ቁጥር 430/97 እና የአፈፃፀም መመሪያው ተሻሽሎ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን በዚሁ አዋጅ ተጠሪነቱ ለቀድሞ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሆነ የመንግሥት ግዥ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲም እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
በመቀጠልም ለመንግስት ንብረት ልዩ ትኩረት ሊሠጥ እንደሚገባ በተሠጠው አስተያየት የዳሰሳ ጥናት ውጤት መሠረት የመንግሥት ግዥና ንብረትን አንድ ላይ እንደገና በማዋሀድ በአዋጅ ቁጥር 649/2001 የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በጰጉሜ 4 ቀን 2001ዓ.ም ተቋቋሞ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀምንና የንብረት አስተዳደሩን እየመራ ይገኛል፡፡


የኤጀንሲው ተልዕኮ፣ራዕይና እሴቶች

ራዕይ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ስርዓትና አፈፃፀም ትራንስፎርም የሚያደርግ ተቋም ሆኖ መገኘት፣

ተልዕኮ

ዘመናዊ የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን በመዘርጋት፣የመፈጸምና የማስፈጸም  አቅም በዘላቂነት በመገንባት፣ ቁጥጥርና ክትትልን በማጠናክር የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ፍትሃዊ ፣ ቀልጣፋ ፣ ውጤታማ እንዲሆን  ግልፅነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፡፡

ዕሴቶች

  1. ለውጥና መልካም አስተዳደር ለውጤት
  2. የህዝብ አገልጋይነትን መላበስ፣
  3. ትኩረት ለዘመናዊ የግዥና ንብረት አስተዳደር ሙያዊ ልቀት፣
  4. የቡድን ሥራ ለውጤታማነት፣
  5. ትኩረት ለባለብዙ ዘርፍ፣
  6. ፍትሀዊነት፣ቅንነት፣ ታማኝነት፣ እና ተጠያቂነት እንዲኖር ተግቶ መስራት

የኤጀንሲው ተግባሮች

ኤጀንሲው ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ተግባሮች ያከናውናል፡-

በመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ፖሊሲዎች፤መርሆዎችና አፋፃፀሞች ላይ የፌደራል መንግስትን ማማከር፤ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደሮች የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት፤
በፌዴራል መንግስት ውስጥ ያለውን የመንግስት ግዥ አፈፃፀም እና የንብረት አስተዳደር ስርአት ተግባራዊነት መከታተል፤ለሚኒስትሩ ሪፖርት ማድረግ እና በ ሕግና በአፈፃፀም ስርአቱን ላይ ማሻሻያ ሀሳቦች ማቅረብ፤
አግባብነት ካላቸው አካላት ጋር በመተባበር የግዥ እና የንብረት አስተዳደር ስልጠና እንዲሁም የግዥና የንብረት አስተዳደር አፈፃፀምን ለመምራት የሚያስፈልገው ችሎታ በሙያው ለመሠማራት ተፈላጊ የሆነውን ፣ማስረጃ ዓይነት እና የሙያው ዕድገት ሊከተል የሚገባው ሂደር መወሰኑን ማረጋገጥ፤
መደበኛ የግዥ ሰነዶች፤አሠራሩን የሚመሩ ቅፆች እና ሌሎች ለግዥ እና ንብረት አስተዳደር አግባብነት ያላቸውን ሰነዶች ማዘጋጀት፤ሥራ ላይ እንዲውሉ እና ወቅታዊ እንዲሆኑ ማድረግ፤
ከተፈቀዱ መደበኛ የግዥ ዘዴዎች፤ሰነዶች፤አሰራሩን ከሚመሩ ቅፆች እና ሌሎች ለግዥ አፈፃፀም አግባብነት ካላቸው ሰነዶች ውጪ ግዥ ለመፈፀም ወይም ከተፈቀዱ የንብረት አወጋገድ ሥርዓቶችና ስልቶች ውጭ ንብረት ለማስወገድ በመንግስት መሥሪያ ቤቶች ጥያቄውን መርምሮ ውሳኔ መስጠት፤
በመንግስት ግዥ ለማሳተፍ ፍላጎት ያላቸው አቅራቢዎች የሚመዘግቡትን የተቀላጠፈ ሥርአት መዘርጋት በአቅራቢዎች ዝርዝር ውስጥ ለመመዝገብ የሚቀርቡ ማመልከቻዎችን መቀበል መመርመር እና የምዝገባውን ዝርዝር ማሠራጨት፤
በዕጩ ተወዳዳሪዎችና በአቅራቢዎች ላይ የመንግስት መስራያ ቤቶች የሚያቀርቧቸውን አቤቱታዎች መርምሮ ውሣኔ መስጠት፤የውሳኔውን ቅጂ ለሚመለከታቸው ማሠራጨት፤
ከመንግስት መሥሪያ ቤቶች ጋር ባደረጉት የግዥ ውል መሠረት ግዴታቸውን ባለመወጣታቸው ስለብቃታቸው ሀሰተኛ መረጃ በማቅረባቸው ወይም በዚህ አዋጅ አንቀጽ ፲፮(፫) እና ፴፪(፪) የተዘረዘሩት ድርጊቶች በመፈፀማቸው ምክኒያት ኤጀንሲው በመንግስት ግዥ አፈፃፀም እንዳይሳተፉ ያገዳቸውን አቅራቢዎች ዝርዝር መያዝና ማሠራጨት፤
ለግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር የሚያገለግል የመረጃ ማሰራጫ እና ክምችት ማቋቋም ማጎልበት መጠበቅ እና ወቅታዊነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ማድረግ
የተቋም እና የሰው ጋር ኃይል አቅም ለማጎልበት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ፖሊሲና ዕቅድ እንዲኖር ማድረግ፤

የሙያና ከሙያ ጋር በተያየዙ አግባብነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የተሠማሩ ሆነው በመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ለመሳተፍ ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር ተቋማዊ ግንኙነት መፍጠር እና ማዳበር፤ስለመንግስት ግዥ አፈፃፀም እነ ንብረት አስተዳደር ጥናት ማካሔድ የአቅም ግንባታ፤ትብብር እንዲኖር ማድረግ፤
ይህ አዋጅና በአዋጁ መሠረት የሚወጡ ደንቦች መመሪያዎች እንዲሁም በሚኒስትሩ የተሰጡት ሌሎች ተግባሮች በትክክል ስራ ላይ መዋላቸውን ማረጋጥ፤

ከመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚቀርብለትን መረጃ መሰረት በማድረግ የመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር ሥርዓት እና መጠን እንዲሁም ንብረት አስተዳደር ጉዳዮች ልዩ መረጃዎችን መስጠት፤
በዚህ አዋጅ በመንግስት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ ላይ በዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚቀርቡ አቤቱታዎችን እንዲያይ ለተቋቋመው ውሳኔ ሰጪ ቦርድ የጽህፈት ቤትና የቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎት መስጠትና የቦርዱን ውሳኔዎች ተግባራዊነት መከታተል፤
አግባብነት ባላቸው የብሔር ክልላዊ መንግስታት አካላት በክልሉ የመንግስት ግዥ አገጻጸም ላ እንዳሳተፉ የታገደ እጩ ተወዳዳሪ ወይም አቅራቢ በፌደራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች ግዥ እንዳይሳተፍ ማድረግ፤
በመንግስት መሥራ ቤቶች አገልግሎት ላይ ለሚውሉ ዋና ዋና ቋሚ ንብረቶች ደረጃ ማውጣት አፈጻጸሙን መከታተል፡፡


የኤጀንሲው ሥልጣን

ኤጀንሲው ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ የሚከተለው ሥልጣን ይኖረዋል፡-

  • ማናቸውም የመንግስት መሥሪያ ቤት ወይም አቅራቢ ሕግ ከሚያዘው ውጪ ስለመፈፀሙ፤ግዥ በትክክል ስላለማከናወኑ የግዥውን አሰራር በትክክል ስላለመፈፀሙ ወይም ስለመመሳጠሩ ጥቆማ የቀረበ እንደሆነ ከግዥው አፈፃፀም ጋር የተያያዙ መረጃዎች፤ሰነዶች፤መዝገቦች እና ሪፖርቶች እንዲቀርቡለት የማዘዝ፤
  • ምስክሮችን የመጥራት፤ምስክሮችና ግዥውን የሚመለከታቸው ወገኖች ቃላቸውን በመሃላ እንዲሰጡ የማድረግ፤የሂሳብ መዝብ፤ፕላን፤ሰነድ እንዲቀርብለት የማድረግ፤
  • ከገበያ ጋር የማይጣጣም ዋጋ በሚያቀርቡ እና ሌሎችም የዚህን አዋጅ እና በሚኒስትሩ የሚወጣውን መመሪያ ድንጋጌዎች፤አቅራቢዎች ወይም በመንግስት ንብረት ማስወገድ ሂደት ተሳታፊዎች ላ በቀረበ አቤቱታ መነሻነት ማስጠንቀቂያ የመስጠት፤ለተወሰነ ወይም የንብረት ማስወገድ ሂደት እንዳይሳተፍ የማገድ፤
  • በመንግስት ግዥ እና ንብረት አስተዳደር አፈፃፀም ላይ በራሱ ፕሮግራም ወይም በሚደርሰው ጥቆማ መነሻነት ኦዲት እንዲካሔድ ማድረግ፤
  • በቂ ምክኒያት ያለ መሆኑን ሲረዳ በዚሁ አዋጅና በግዥ መመሪያው ከተፈቀዱ የግዥ ሥርዓቶች ውጪ ግዢ ለመፈፀም ከመንግስት መስሪያ ቤቶች በሚቀርቡ ጥያቄዎች መሰረት እንዲፈፀም መፍቀድ፡፡