The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራርና ሙስናን መከላከል በሚመለከት ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሥነ-ምግባር  የተሞላ አመራርና ሙስናን የመከላከል ተግባርን በሚመለከት ለኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከግንቦት 11—12/2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡
አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በፕሮግራሙ መክፈቻው ንግግር ላይ እንደተናገሩት  ሥልጠናው ለኤጀንሲው የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሰጥ የተፈለገበት ምከንያት በመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሠረት የአገሪቱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ከሚፈስባቸውና በዚያው ልክ የመንግስት ገንዘብ ለብክነትና ለሙስና የተጋለጡ ናቸው ተብለው ከተፈረጁት የሥራ ዘርፎች አንዱ የመንግስት ግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አስተዳደር በመሆኑና ይህም የተዘረጋውን የህግ ማዕቀፍና የአሰራር ሥርዓት ተከትሎ የስራ ዘርፉ ከሙስና እና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ሆኖ በጥራትና በሚፈለገው ጊዜ እንዲከናውንና ለሀገሪቱ ልማት እና መልካም አስተዳደር የበኩሉን አሰተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚጠበቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የመንግስት ግዥ የሚፈጸመው በእያንዳንዱ ባለበጀት መ/ቤት እንደመሆኑ መጠን እያንዳንዱ ግዥ ፈጻሚ መ/ቤት ሕጎችን በማክበር በመልካም ሥነ-ምግባር መፈጸም ያለበት ሲሆን፣ ኤጀንሲያችንም በየመ/ቤቱ የሚከናወነውን የግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓቱን ጠብቆ ስለመሆኑ ክትትልና ቁጥጥር ከሚያደርጉት አካላት ጎራ ስለሆነ የተሰጠውን ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ከሙስና በጸዳ ሁኔታ የሙያውን ሥነ-ምግባር በመከተል ተግባራቱንና ኃላፊነቱን መወጣት እንደሚኖርበት አስረድተዋል፡፡
አቶ ወንድይራድ ሰይፉ በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል የቡድን አሰተባባሪ የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት እና ፀረ-ሙስና እንቅስቃሴ በአንድ ተቋም ሩጫና ጥረት የሚቀረፍ ሳይሆን አጠቃላይ በሆነ መልኩ ፖለቲካል ኢኮኖሚውን መዋቅራዊ አደረጃጀት ለመቀየር በሚያስችል ሁኔታ በየደረጃው  ያሉ ተቋማትና ማህበረሰቡ በተደራጀ መልኩ የሚያደርጉትን የባለቤትነት ስሜት የታከለበት ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ፈንታ ማንደፍሮ በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ቴክኒካል አድቫይዘር ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ስለሥነ-ምግባር ምንነት? ለምን ሥነ-ምግባር  የተሞላ አመራር ላይ እናተኩራለን? ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራር ማለት ምን ማለት ነው?ምንስ ይጠይቃል? ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራር መርሆዎችና ክህሎቶች ምንድን ናቸው? መገለጫና ባህሪዎቹ እንዲሁም የሚገጥሙትስ ተግዳሮቶች ምንድን ናቸው? ሥነ-ምግባር የተሞላ አመራር፣ሙስናን የመከላከል ተግባር ቁርኝታቸውና አመልካች ነጥቦቹ  እና ሌሎች አጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ነባራዊ ምሳሌ በመስጠት ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል ፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለ2 ቀናት በቆየው በሥነ-ምግባር የተሞላ አመራርና ሙስናን መከላከል በሚመለከት በተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት