The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

መንግስት ፋይናንስ፣የግዥና የንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ ውይይት ተካሄደ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመንግስት ፋይናንስ፣የግዥና የንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆችን በተመለከተ ጥር 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መሰብሰቢያ አደራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
አቶ ፀጋዬ አበበ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የስብሰባው ዋና ዓላማ የማሻሻያ ሥራ እየተሰራላቸው ባሉት በፌዴራሉ የመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና በመንግሥት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አዋጅ ዙሪያ የዘርፉ ፈጻሚ ከሆኑት ከፌዴራል መንግስት መስራ ቤቶች የተዉጣጡ ባለሙያዎችና የስራ ኃለፊዎች ጋር በመመካከር የጋራ ግንዛቤን ማሳደግና በህግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ላይ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን ገንቢ ግብአት እንዲሰጡ በመጠየቅ የዉይይት መድረኩን አስጀምረዋል፡፡
በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር እና ግዥ አፈጻጸም ውስጥ ሊከሰት የሚችል የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን በአገር ደረጃ ከምንጩ ለማድረቅ እና ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሠራርን እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተጀመረውን ጥረት ከዳር ለማድረስ ከፈጻሚ የመንግስት አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠበቅ ኣክለዉ ገልጸዋል፡፡
አቶ ብርሃኑ ታደሰ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ የፌዴራል መንግስት የፋይናንስ ማሻሻያ ረቂቅ ሕጎችን ዋና ዋና ነጥቦችን በማንሳት ስለማሻሻያው ዓብይ ምክንያቶች፣ስለተሻሻሉ ዋና ዋና ድንጋጌዎች፣ከፕሮገራም በጀት አንጻር ስለተሻሻሉ ድንጋጌዎች አና በአፈጻጸም ስለአጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጆንሴ ገደፋ በበኩላቸዉ በአዲሱ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ረቂቅ ውስጥ ስለተካተቱ ዋና ዋና ለውጦች እና ከግዥ የገንዘብ ጣሪያ እና ከግንባታ ሥራ አፈጻጸም መመሪያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች፣ ሰለዓለም ዓቀፍ ግልጽ ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ፣በግንባታ ሥፍራ ላይ ከሚገኙ ማቴሪያሎች ክፍያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያና ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ገለጻ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለአንድ ቀን በቆየው የመንግስት ፋይናንስ፣የግዥና የንብረት አስተዳደር ረቂቅ አዋጆች ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ከተለያዩ ፌዴራል መስራ ቤቶች የተዉጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡