The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ኤጀንሲው ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር የውይይት መድረክ አዘጋጀ


የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በመልካም አሰተዳደር ንቃናቄ ዙሪያ ጥር 20 ቀን 2008ዓ.ም. በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ውይይት አደረገ፡፡
የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጆንሴ ገደፋ እንደተናገሩት የስብሰባው ዋና አጀንዳ በመንግስት የግዥ እና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ላይ ሊደረጉ የታሰቡ ማሻሻያዎችን እና ተሻሽለው ሥራ ላይ የዋለው በተለይም የግንባታ ዘርፍ ማነቆዎች ተብለው የተለዩ ጉዳዮች፣ከመንግስት የግዥ አፈጻጸም ዙሪያ የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋሞች መብትና ግዴታዎች፣በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ የሚቀርቡ አቤቱታዎች እና የውሳኔ ሃሳቦች እንዲሁም በመንግስት የግዥ አፈጻጸም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን የሚያጋጥሙያቸዉ የገበያ ትስስር ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም በዚህ መድረክ የተገኙት አካላት በአጀንዳዎቹ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ለማሻሻያው ጠቃሚ የሆኑ ግብአቶችን በመስጠትና ለወደፊቱም በተመሳሳይ መልኩ የተለያዩ መደረኮችን በጋራ በማዘጋጀት ውይይቱ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልጸው ውይይቱን በይፋ ከፍተዋል፡፡
አቶ ነብዩ ኮከብ በፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ውስጥ ስለተካተቱ ዋና ዋና ለውጦች እና ከግዥ የገንዘብ ጣሪያ እና ከግንባታ ሥራ አፈጻጸም መመሪያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች፣ ሰለዓለም ዓቀፍ ግልጽ ጨረታ የገንዘብ ጣሪያ፣ በግንባታ ሥፍራ ላይ ከሚገኙ ማቴሪያሎች ክፍያ ጋር በተያያዘ ስለተደረጉ ማሻሻያዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
አቶ ትግስት ደበበ በፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት  ዳይሬክተር በፌዴራል መንግስት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መብትና ግዴታዎች፣በአቅራቢዎች በኩል ሰለሚታዩ ግድፈቶች፣በፌዴራል መንግስት ግዥ ዙሪያ በአቅራቢዎች በመንግስት መ/ቤቶች ላይ ሰለሚቀርቡ አቤቱታዎች እና በመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ ስለሚቀርቡ የጥፋተኝነት ሪፖርቶችን በመዘርዘር አሰረድተዋል፡፡
አቶ ዘሪሁን አለማየሁ በፌደራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ የገበያ ልማትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው በመንግስት የግዢ አፈፃፀም ዙሪያ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ያጋጠማቸው ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በቀረበው ገለጻ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ለአንድ ቀን በቆየው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር የተካሄደ የህዝብ ክንፍ የውይይት መድረክ ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ከጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የመጡ ተሳታፊዎች እና የተለያዩ መ/ቤቶች ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡