The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የፌዴራል የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመልካም አስተዳደር ንቅናቄ ዙሪያ ላይ ያተኮረ ውይይት ጥር 19 ቀን 2008 ዓ.ም በአሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል አካሄደ፡፡
የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የውይይቱ ዋና ዓላማ የማሻሻያ ስራ እየተሰራ ባለው በፌደራሉ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ዙሪያ የዘርፉ ባለድርሻ ከሆነው የንግዱ ህብረተሰብ አባላት ጋር በመመካከር የጋራ ግንዛቤን ማሳደግና በህግ ማዕቀፉ ማሻሻያ ላይ የንግዱ ህብረተሰብ አባላት የበኩላቸውን ግብዓት እንዲሰጡ በማሰብ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የተዘረጋውን የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ሥርዓት በትክክል ተግባራዊ በማድረግ ተገልጋዮችን ማርካት ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ባለፈ የመልካም አስተዳደር መገለጫ አንዱና ዋነኛ ምሰሶ መሆኑን ገልፀው የውይይቱ ተሳታፊዎችም በቀረቡት አጀንዳዎች ላይ በንቃት እንዲከታተሉና እንዲሳተፉ በማሳሰብ  መድረኩን  በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በመቀጠልም በፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ግዥ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ነቢዩ ኮከብ በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ የተካተቱ ዋና ዋና ለውጦችና ከግዥ የገንዘብ ጣሪያ እና ከግንባታ ስራ የአፈፃፀም መመሪያ ጋር በተያያዘ አዲስ በተጨመሩና በተደረጉ ማሻሻያዎች ላይ በዝርዝር ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡ 
አቶ ነጋሽ ቦንኬ የመንግሥት ግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ተ/ዳይሬክተር በበኩላቸው የፌዴራል መንግስት የግዥና ንብረት አስተዳደር የሚመራባቸው የህግ ሰነዶች በፌደራል መንግስት የግዥ ሂደት አቅራቢዎች በመንግስት መ/ቤቶች ላይ የሚቀርብ አቤቱታ እና መንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ የሚቀርብ የጥፋተኝነት ሪፖርት፣በተጫራቾች የሚቀርቡ የአቤቱታ መነሻዎች፣የአቤቱታ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት፣ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪ ውሳኔ ሰጪ ቦርድ አባላትና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ አበበ አወያይነት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች፣አስተያየቶችና ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎችና ሃሳቦች በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የበላይ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር  አቶ ፀጋዬ አበበ በተሳታፊዎች የተሰጠው አስተያየት ገንቢ እንደሆነና የተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተገቢ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቀረ የሚባል አስተያየት፣ ጥያቄና ሃሳብ ካለ ተሳታፊዎች በፅሁፍ፣ በግንባርና በኢሜይል ለኤጀንሲው በማቅረብ ግብዓቶቹን መጠቀም እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡