The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የግንባታ ስራን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ላይ ውይይት ተደረገ

የአፈፃፀም መመሪያውም ከጥር 01 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በሚሻሻለው የግንባታ ስራ ረቂቅ የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ላይ ታህሳስ 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ ውይይት አደረገ፡፡
የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ የውይይቱን ሪቂቅ ሰነድ ሲያቀርቡ እንደተናገሩት ዓላማው በአዋጅ ቁጥር 649/2001 ዓ.ም በግዥ ዙሪያ አላሰራ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አቅራቢው በግንባታ ሥራ የግዥ የብቃት መስፈርት አወሳሰንና ትርጓሜን፣አጠቃላይና ተዛማጅ የሥራ ልምድን፣የፋይናስ አቋምን፣ዓመታዊ የተርን ኦቨር መጠንን፣በግንባታ ሥራ ላይ የሚሰማሩ ባለሙያዎች የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን፣ የግንባታ ሥራ መሟላትን በተመለከተ ሠፋ ያለ ማብራሪያና ገለፃ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ከአንድ በላይ ንዑሳን የግንባታ ሥራዎች (lots) በተካተቱበት ግዥ ላይ የልምድ አያያዝን፣ለህንፃ ግንባታ ሥራ የሚጠየቅ ዝቅተኛ መስፈርት፣ለድልድይ ግንባታ ሥራ የሚጠየቅ ዝቅተኛ የግንባታ መስፈርት፣የመንገድ ፕሮጀክቶች አመዳደብ በንጣፍ ዓይነት፣ለመንገድ ፕሮጅቶች የግንባታ ሥራ የሚጠየቅ ዝቅተኛ መስፈርት፣እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሠጥተዋል፡፡
አቶ ጆንሴ የመመሪያው አንቀፅ 22(1) መንደርደሪያ ተሰርዞ የመንግስት መ/ቤት የምክር አገልግሎት የግዥው ግመታዊ ዋጋ ከብር 900,000 (ዘጠኝ መቶ ሺህ ብር)የሚበልጥ በሚሆንበት ጊዜ በምክር አገልግሎቱ አቅርቦት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች በመጋበዝ ጥሪ ማድረግ ይኖርበታል በሚለው ሀሳብ መካተቱን ገልፀዋል፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር በክቡር አቶ አብዱልአዚዝ መሀመድ እና በሚንስትር ዴኤታው በክቡር  አቶ አለማየሁ ጉጆ አወያይነት ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና  አስተያየቶች  የተነሱ ሲሆን ማብራሪያ ለሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸው የግዥ አፈፃፀም  መመሪያውም ከጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈፃሚ እንደሚሆንም ኃላፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ለግማሽ ቀን በቆየው የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲና የባለድርሻ አካላት  የግንባታ ስራን ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ የፌዴራል መንግስት የግዥ አፈፃፀም መመሪያ ውይይት ላይ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡