The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

28ኛዉ የዓለም ኤች አይቪ/ኤድስ እና 25ኛዉ የጸረ-ጾታ ጥቃት ቀን ተከበረ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እና ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመተባበር የ28ኛውን ዓለም አቀፍ የኤድስ እና 25ኛውን ዓለም አቀፍ የጸረ—ጾታ ቀን ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት መሰብሰቢያ አዳራሽ አከበረ፡፡
አቶ ከዋኒ ይብራ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የጤናና የሥነ—ምግብ ፕላን ባለሙያ በዓለም ለ28ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ27ኛ ግዜ የሚከበረውን የኤድስ ቀንን በማስመልከት "አንድም ሰው በኤች. አይ. ቪ. እንዳይያዝ ኃላፊነታችንን በመወጣት የሃገራችንን ህዳሴ እናሳካ!!" ከሚለው መሪ ቃል ተነስተው ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ ስለ ኤች. አይ. ቪ. ኤድስ አጠቃላይ  ሁኔታዎች፣ስለ ህክምና፣ድጋፍና እንክብካቤ፣ስለ መከላከልና መቆጣጠር፣ ስኬቶችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ስለ ቀጣይ ሥራዎች ገለጻ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም ስለ ቀይ ሪቫን ትርጉም፣የኤድስ ቀን ለምን በየዓመቱ ይከበራል? ስለ ኤች. አይ. ቪ. ምንነት፤ ስለ ምልክቶቹና ስሜቶቹ፤በዓለምና ከሰሃራ በታች ባሉት ሃገራት የኤች. አይ. ቪ. ሁኔታ እና በኢትዮጵያ ስለ ኤች. አይ. ቪ. አመጣጥና ክስተት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በፌዴራል ፍትህ ሚኒስቴር አቃቤ ህግ ባለሙያ የሆኑት ወ/ት ፋሲካ አበራ በበኩላቸው ስለ ሴቶች መብትና ጾታዊ ጥቃት፣ስለ ሰብአዊ መብት ምንነት፣ሴቶች በዋናነት የዕኩልነት መብትና ከሴትነታቸው ከሚመነጩ ፍላጎቶች አንጻር ልዩ ጥበቃ የማግኘት መብት ያላቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
አሰልጣኟ ስለ ጥቃት /violence/ ምንነት፣ በተዛባ የሥርዓተ—ጾታ ግንዛቤና አስተሳሰብ ምክንያት በተለያየ መንገድ የሚፈጸም ጾታን መሰረት ስላደረገ ጥቃትና አይነቶቹ፣ጾታዊ ጥቃት በማንና የት እንደሚፈጸም፣ ስለሚያስከትለው ውጤት፣ስለ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ ጉዳትና መንስኤዎቹ፣ሰለ ህግ ማዕቀፎች፣በአጠቃላይ ሴቶች የህብረተሰቡ ግማሽ አካል እንዲሁም የሁሉም እናት በመሆናቸው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት መሰረታዊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን በማስተዋል ሁላችንም ጾታዊ ጥቃትን የመከላከል ሃላፊነታችንን እንወጣ! በማለት ገለጻ አድርገዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለግማሽ ቀን በቆየው ከመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እና ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ የተዘጋጀው የዓለም የኤድስ እና የዓለም አቀፍ የጸረ—ጾታ ቀን ላይ የሶስቱም መ/ቤት ሃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት