The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ኤጀንሲው በአማካሪ ባስጠናው መመሪያ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ

በፌደራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለክልሎችና ለከተማ መስተዳድሮች በአማካሪ ባስጠናው SIMPLIFIED WEREDA SYSTEM የግዥ አገልግሎት መመሪያ የመጀመሪያ ረቂቅ ዙሪያ በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከመጋቢት 28–29 ቀን 2007 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ተሰጠ፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ም/ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ—ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የዉይይት መድረኩ ዋና ዓላማ ለሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች SIMPLIFIED WEREDA SYSTEM የግዥ አገልግሎት መመሪያ በመጀመሪያ ረቂቅ ዙሪያ የግንዛቤ መስጨበጫ ሥልጠና ለመስጠትና የማሻሻያ ግብዓቶችን ከተሳታፊዎች ለማሰባሰብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በመቀጠልም ም/ዋና ዳይሬክተሩ ሁሉም ወረዳዎች ሊጠቀሙበት የሚችሉ አንድ ወጥ የሆነ ቀለል ያለ የወረዳዎችን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የግዥ አገልግሎት መመሪያ ለማዘጋጀት እንደሆነ ጠቁመው፤በናሙና ዳሰሳ ጥናቱም የተለያዩ ያጋጠሙና ሊያገጥሙ የሚችሉ ችግሮች ምን እንደሆነ? በእነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያለንን አስተያየት መስጠት፤ ጥያቄ በመጠየቅ፣  ሥራ ላይ በምናውልበት ጊዜ ሊያጋጥሙን የሚችሉ ስጋቶችን ማንሳት እንዳለባቸው በመግለፅ ለዕለቱ የቀረበውን የዳሰሳ ጥናት ዉይይት አስጀምረዋል፡፡
የላይፍ አማካሪ ድርጅት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ዳምጠው ወልዴ የዳሰሳ ጥናቱ በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳደሮችን በማከለ 53 በሚሆኑ የናሙና ወረዳዎች በመውሰድ የተጠና SIMPLIFIED WEREDA SYSTEM የግዥ አገልግሎት መመሪያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የቀረበው ጥናት የመጨረሻና ያለቀለት አለመሆኑንና ከተሳታፊዎች ብዙ ግብዓት እንደሚገኝ በመጥቀስ ወደ ገለፃ ግብተዋል፡፡
ከሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች የተውጣጡ የግዥና ንብረት አስተዳደር ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የቀረበው ቀለል ያለ የግዥ አገልግሎት መመሪያ አግባብ መሆኑን ጠቅሰው ለወረዳዎች በሚያመች መልኩ መዘጋጀቱ ብዙ የወረዳዎችን ችግር እንደሚቀርፍ ይታመንበታል በማለት ገልፀዋል፡፡

በመቀጠልም ቀለል ያለ የግዥ አገልግሎት መመሪያ ዙሪያ በተዘጋጀው ዉይይት መድረክ ላይ ተሳታፊዎች ሰፋ ያለ የማሻሸያ ግብዓቶችን በማንሳት፣ግልፅ ያልሆነላቸውን ጥያቄ በመጠየቅና አስተያየቶችን በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡
ለሁለት ቀናት በቆየው የፌደራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በአማካሪ ባስጠናው SIMPLIFIED WEREDA SYSTEM የግዥ አገልግሎት መመሪያ የመጀመሪያ ረቂቅ ዉይይት መድረክ ላይ ከ100 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት