The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በመንግሥት ግዥ ዙሪያ ሥልጠና ሰጠ

የመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ ዙሪያ ከሁሉም የፌዴራል መ/ቤቶች ለተውጣጡ ሰልጣኞች ከህዳር 29 እስከ ታህሣሥ 3/2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ለአምስት ቀናት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡

ሥልጠናው በዋናነት በፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች በግዥ ሥርዓትና አጠቃቀም ላይ ያለውን የግንዛቤ እጥረት ለመቅረፍና ግዥ ከፍተኛውን የመንግሥት በጀት ስለሚይዝ ጥንቃቄ አንደሚያስፈልገው እንዲሁም ከሠልጣኞች ልምድ ለመውሰድና ከአሰልጣኙ መ/ቤት ደግሞ ቲዎሪን በመውሰድ ሁለቱን በማቀነባበር የተሻለ የግዥ ሥርዓት ለማስፈን አብሮ መማማር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል፡፡

አሰልጣኞቹ አቶ ታደለ ነጋሽ የግዥና ንብረት የኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ አቶ ዘለቀ ታፈሰ ከፍተኛ የግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል ባለሙያ እና አቶ ታደሰ ከበደ ረዳት የግዥ ጥናትና መረጃ ትንተና ባለሙያ ስለ መንግሥት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ የመንግሥት ግዥ ምንድነው? የመንግሥት ግዥ ስለሚመራባቸው ሕጐች፣ ስለዓለም አቀፍ ግዴታዎች፣ ስለመንግሥት ግዥ መርሆዎች፣ ተግባርና ኃላፊነት፣ በመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ሊኖር ስለሚገባ ሥነ ምግባር፣ ስለ ግዥ ዕቅድና ዑደት፣ ስለግዥ ዓይነቶች፣ ስለ ጨረታ፣ ስለ ግዥ ዘዴዎች፣ ስለ ቴክኒክ ፍላጐት መግለጫ አዘገጃጀት፣ ስለ መደበኛ ጨረታ ሰነድ ይዘትና አጠቃቀም፣ ስለ ጨረታ ግምገማ፣ ስለ ቅድመ ብቃት ማረጋገጫ ጨረታ እና ሰለ አገልግሎት ግዥ በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ከየመ/ቤቱ የተውጣጡ ሰልጣኞች በቆይታቸው ሥልጠናው ጥሩ አቅም እንደፈጠረላቸውና የነበረባቸውን ክፍተት ለመሙላትና ከሥልጠናው ያገኙትን ዕውቀት በየመ/ቤታቸው ወደ ተግባር ለመለወጥ አጋዥ እንደሚሆንላቸውም ገልጸዋል፡፡

ለአምስት ቀናት በቆየው የመንግሥት ግዥ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሠልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት