The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ከመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚስተዋል ሌብነትን የሚያስወግድ አሠራር እየተዘረጋ ነው

"ከመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ጋር በተያያዘ የሚስተዋል ሌብነትን የሚያስወግድ አሠራር እየተዘረጋ ነው" የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 24/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ከሀገሪቱ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እሰከ የመንግሥት ተቋማት የሚስተዋለው ውስብስብ ሌብነትና ብልሹ አሠራር እያደረሰ ያለው  ኪሳራ ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ እንደኾነ ይነገራል። "የሰለጠነ፣ ስብዕናው የተገራ፣ የችግር መፍቻ ቁልፍ ማዕከል ነው "ተብሎ በሚታመንበት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሳይቀር ከግዥና ንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮች መኖራቸው ደግሞ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
የኢፊዴሪ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀጂ ኢብሳ እንደሚሉት ከጠቅላላው የሀገሪቱ ዓመታዊ በጀት ከ65 በመቶ በላይ የሚኾነው ገንዘብ ለግዥ ይውላል። ይኽ ከፍተኛ መዋለንዋይ የሚፈስበት ዘርፍ በሌብነትና በብልሹ አሠራር መተብተቡ  ሀገርን ዋጋ እያስከፈለ ነው። ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ከግዥና ከጫራታ ጋር በተያያዘ የሚፈጠር መስተጓጎል ዋነኛው ምክንያት ነው የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ በአንድ ወቅት በሀገሪቱ የሚገነቡ የመንግሥት ፕሮጀክቶች  በታቀደላቸው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት ብቻ  እስከ 43 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ጠይቀዋል ነው ያሉት።  በሀገሪቱ ለግዥ ከፍተኛ  በጀት ከሚበጀትላቸው ተቋማት ዩኒቨርሲቲዎች ቀዳሚ መኾናቸውን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከግዥና ሃብት አስተዳደር ላይ የሚስተዋልባቸውን ብልሹ አሠራር ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ብለዋል።  የአሠራርና የእውቀት ክፍተቶችን በመሙላት፣ ኾን ተብሎ የተፈጠረን ብልሹ አሠራር ላይ ደግሞ ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ነው የተናገሩት።
በፌዴራል ደረጃ ብቻ 450 ተቋማት ላይ ከግዥ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ሕገወጥ ድርጊት እርምጃ ተወስዷልም ነው ያሉት።  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ባላቸው የግዥና ንብረት አስተዳደር ጥራት ወስብስብ ችግር ያለባቸውን "ቀይ"፣ መጠነኛ ቸግር ያለባቸውን "ቢጫ"፣ጥሩ አሠራር ላይ ያሉትን ደግሞ "አረንጓዴ" እያሉ ደረጃ በመስጠት ከችግራቸው እንዲላቀቁ የግንዛቤ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።  በዚህም በተደጋጋሚ በተደረገ ስልጠናና የማስተካከያ እርምጃ አንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከቀይ ወደ አርንጓዴ መሸጋገር መቻላቸውን አንስተዋል።
"አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣አርሲና ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲዎችን  ከቀይ ወደ አረንጓዴ የተሸጋገሩ" ሲሉም በምሳሌነት ጠቅሰዋል።  በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ከጨረታ እሰከ የሚገዛው እቃ የጥራት ችግር ሀገርን ኪሳራ ላይ የሚጥሉ ውስብስብ ችግሮች አሉ የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ በተላይም ከተጫራች ጋር መደራደር፣ጨረታን ማዘግየት፣ከሕግ ውጭ ውስን ተጫራቾችን ብቻ ማሳተፍ፣የጨረታ ሰነድ አልቋል ማለት እና ሌሎችም ሕገወጥ ድርጊቶች የመንግሥት ሃብትና ንብረት በብልሹ አሠራር እየተዘረፈ ነው ብለዋል።
የመንግሥትን የግዥ ሥርዓት የመዘረጋትና  የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለስልጣን መስሪያቤትም ሕገወጥነትን ለመከላከል  ተቋማት የሚያወጡት ጨረታ በኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሥርዓት እንዲኾን የሚያስገድድ አሠራር ዘርግቷል ብለዋል።  ይህ ሥርዓት የሚፈጠርን ሌብነትና ብልሹ አሠራር የሚቀርፍ ይኾናል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ በቅርቡ 115 የመንግሥት ተቋማት ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግብይት ሲስተም ይገባሉ ብለዋል።  የሚጀመሩ ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜና በጥራት እንዲጠናቀቁ የሚወጡ ጨረታዎች ሥራ ተኮር እንጂ ሰው ተኮር እንዳይኾኑ
ስለሀገሩ የሚጨነቅ ፣ ሀገሩን የሚወድና ስብዕናው የተገነባ ዜጋ መፍጠር ይገባል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ የአሠራር ሥርዓትን ከመዘርጋት ባሻገርም የአሠራር ግድፈትን ለመቅረፍ ስልጠናና ግንዛቤ ፈጠራ ላይ እየተሠራ ነው ብለዋል።  ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋርም የጋራ ፎረሞችን እያዘጋጁ ምርምርም ምክክርም እየተደረገ መኾኑን ነው የተናገሩት።