The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ባለስልጣኑ ከክልል አቻ የግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ አካላት ጋር ተወያዬ

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከክልል አቻ የግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም እንዲሁም የማዕከል ግዥ ፈፃሚ አካላት ጋር በባህርዳር ከተማ የምክክር መድረክ እያከናወነ ይገኛል፡፡
የምክክር መድረኩ ከሐምሌ 25 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከሁሉም ክልሎች (ከትግራይ ክልል በስተቀር) የተውጣጡ የግዥ ተቆጣጣሪነት ሚና ያላቸው ተቋማት እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
በምክክር መድረኩ የክልሎች የቁልፍ ግዥ አፈፃፀምና ተሞክሮ፣ የክልሎች ተቆጣጣሪ አካላት የወረዳ ግዥ ኦዲትና የካልም (CALM) ወረዳዎች ኦዲት አፈፃፀም ሪፖርትና ተሞክሮ፣ በማዕቀፍ ግዥ አላማና መርህ፣ የመንግስት ግዥ አገልግሎት ሰጭ አካላት ኃላፊነትና ሚና፣ የመንግስት ግዥ አፈፃፀም እና የንብረት አወጋገድና ተሞክሮ የሚቀርብ ሲሆን በተጨማሪም ከዓለም ባንክ በተጋባዥ እንግዶች የMethodology for Assessment of Procurement System-II (MAPS-II) ሪፖርትና ዋና ዋና ችግሮች ቀርበው፤ የMAPS-II ውጤት ይፋ ማድረግ ስራ ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባለስልጣኑ ከክልል አቻ የግዥና ንብረት ተቆጣጣሪ ተቋም እንዲሁም የማዕከል ግዥ ፈፃሚ አካላት ጋር ከሚያከናውነው ምክክር መድረክ የልምድ ልውውጥ ከመደረጉም ባለፈ ጥሩ ግብአቶች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የመንግሥት በጀት ውስን ነው። ይሄ ውስን ሀብት የሚሰበሰበው ከእያንዳንዷ እናት መቀነት ተፈትቶ ከታክስና ግብር ነው። በመሆኑም በአግባቡ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ለሀገር ልማትና ዕድገት መዋል እንዳለበት ይታመናል። በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱ የሚመደበውን በጀትም በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ይገባል።

የመንግሥት ግዢዎች ፣ ለግንባታ የሚወጣ ወጪ፣ ትላልቅና ትናንሽ ፕሮጀክቶች ግንባታ በሚካሄድበት ጊዜ ፣ ወጪና ጉልበት ቀናሽ በሆነ መልኩ ጥራታቸውን የጠበቁ መሆን አለባቸው። ሁሉም የሀገር ሀብት የሁሉም ዜጋ ሀብትና ንብረት ነውና ይሄንኑ ውስን ሀብት በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ይሆናል።
ይሁን እንጂ አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥት ሀብትና ንብረት አለአግባብ ሲባክን ይታያል። በእውቀት ማነስ ፣ በቸልተኝነት፣ ወይም ደግሞ ወደ ግለሰቦች ኪስ እንዲገባ ታስቦና ታቅዶ የገንዘብ ብክነት ሲፈጸም ይስተዋላል። ይህን የሚመለከት ሠራተኛ፣ ተቆጣጣሪ እና ኃላፊ ብልሹ የሆነ አሠራር ሲኖር ሕግና ሥርዓት እንዲይዝ ማድረግ ፤ ከዚህም አለፍ ብሎ እርምጃ እንዲወሰድ ጭምር መሥራት አለበት ። ነገር ግን አሁን በሚታየው ሁኔታ የሚባክነው የመንግሥት ሀብት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ እንዳልሆነ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የሚገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ።
የዚህም ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚጠቀሰው የመንግሥት መሥሪያ ቤት አሠራርን ያለማወቅና ከብቃት እንዲሁም ክህሎት ማነስ ጋር ተያይዞ ነው። የመንግሥት የአሠራር ሥርዓትን ባለመከተል፣ በቸልተኝነት እና በድፍረት እየተፈጸመ ያለ የአሠራርና የሕግ ጥሰቶች በመኖራቸው ምክንያት ነው ፡፡
በመሆኑም ለተቋማት የሚመደብ በጀት ፤ ለፕሮጀክቶች የሚመደብ ገንዘብ በአግባቡና በወቅቱ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይገባል። ለዚህም የቅርብ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ በአጥፊዎች ላይም አስተማሪ ቅጣት መውሰድ ያስፈልጋል። ብልሹ አሠራርን በማጋለጡ ሂደት በተለይ ደግሞ የውስጥ እና የውጪ ኦዲተሮች ትልቅ ኃላፊነትና የሕዝብ አደራ አለባቸው። የእያንዳንዱን ተቋም የፋይናንስ ሥርዓት በመመርመር ሪፖርት ማድረግ፣ ብልሹ የሆኑ አሠራሮችንም ማጋለጥና ለነገ ትምህርት እንዲወሰድባቸው ማድረግ ይገባቸዋል ።
ከዋና ኦዲተር ባገኘነው መረጃ መሠረት፤ አሁን ባለው ሁኔታ የመንግሥት ተቋማት ያለአግባብ ወጪ ሂሳብ ግኝቶች እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አይደለም። የተሟላ የወጪ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ የሚመዘገብ ሒሳብ፣ ደንብና መመሪያን ሳይከተሉ ግዥዎች መፈጸም ፣ ማስረጃ ሳይኖር በወጪ የተመዘገበና ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የማይቻል የወጪ ሂሳብ ግድፈቶች የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ከ2008 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ያለውን በንጽጽር ሲታይ በ2008 ዓ.ም ያለአግባብ የወጣው ወጪ 826 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ሲሆን ከስድስት ዓመት በኋላ አሁን ይሄ ቁጥር ወደ አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር አሻቅቧል ፡፡ ይሄ ሲታይ ያለአግባብ የሚወጣው ወጪ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ። ይህም የመንግሥት ሀብት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዳልዋለ የሚያመላክት ነው። በመሆኑም ተቋማትን የሚመሩ አካላት በየጊዜው በኦዲቱ የሚሰጣቸውን የማሻሻያ ሃሳቦች መነሻ በማድረግ እርምጃዎችን ከስር ከስር መውሰድ አለባቸው።
አሁን እየታየ ያለው ከጊዜ ወደ ጊዜ ከመስተካከል ይልቅ የሕግ ጥሰቶች፣ የግዥ ሥርዓቱን ተከትሎ ያለመሄድ ሁኔታ እየጨመረ ነው። በመሆኑም የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት በየተቋማት ያሉትን ችግሮች በመለየትና የሂሳብ ግኝቶችን ወደ አደባባይ በማውጣት ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የፋይናንስ ሕግና ሥርዓትን ተከትለው የማይሠሩ ወይም ያልሠሩ ተቋማትን የኦዲት ሪፖርት ለፓርላማው ከነስማቸውና ጉድለታቸው በማቅረብ በአደባባይ ማጋለጥ ጀምሯል። ይሄ ይበል የሚያሰኝ ጅምር ነው ። ሆኖም ግን በቂ ነው ማለት አይደለም።

አሁንም ቀጣይ ሥራዎች መኖር አለባቸው። ከኦዲት ግኝት ሪፖርቱ በመነሳት ጉዳዩ የሚመለከተው አካልም መውሰድ የሚገባውን ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ አለበት። በሕግ አግባብ መጠየቅ ያለበት አካል ካለም ሳይሸፋፈንና የስልጣን ደረጃው ሳይለይ በሕግ አግባብ ተጠያቂ መደረግ አለበት። ይሄም ልክ እንደ ኦዲት ሪፖርቱም ውጤቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም ለሕዝቡ መግለጽ ያስፈልጋል።
መወሰድ በሚገባው ልክ እርምጃ ካልተወሰደም የኦዲት ግኝት መኖሩን ያሳወቀው ዋና ኦዲተር የሥራውን ውጤት ቢያቀርብም እርምጃ መውሰድ የሚገባው አካል ግን ኃላፊነቱን አልተወጣም ሲል የተቋማቱን ስም በግልጽ ለፓርላማው ማሳወቅ ይኖርበታል። የዚህ ጉዳይ አስፈላጊነት አንዱ ከሌላው እንዲማር ለማድረግ ነው። ስለዚህ በቀጣይ ዋናው ኦዲተር አሁን ካደረገው እርምጃ አለፍ ብሎም በዚህ ልክ ሥራቸውን ያልሠሩና ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎችን ማጋለጥ ይገባዋል። የመንግሥትና የሕዝብ ገንዘብና ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ያደረጉና ለግል ጥቅማቸው ያዋሉትንም ማጋለጡን አጠናክሮ መቀጠል አለበት! የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ግኝቶቹን ተከትሎ አስተማሪ እርምጃ መውሰድና ማስተካከል ለነገ ይደር የማይባል ሥራ ሊሆን ይገባል!