The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በግዥ አፈጻጸምና ንብርት አስተዳደር ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በሀገራችን ከሁሉም (ከትግራይ ክልል ዉጪ) ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በግዥ አፈጻጸምና ንብርት አስተዳደር ዙሪያ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶች፤ በወቅታዊ የገበያ ሁኔታ እና በመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 23 እና 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለሶስተኛ ዙር የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል፡፡ የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ ግልፅ፣ ዘመናዊ ቀልጣፋና ውጤታማ የመንግስት ግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደር ማስፈን፣ የመንግስትን ንብረት በጥንቃቄ የመያዝ፣ የመጠቀምና የመቆጣጠር እንዲሁም ንብረቱ አገልግሎቱ ሲያበቃ በወቅቱና በተገቢው መንገድ እንዲወገድ ማስቻል  ነው፡፡

የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ትዉልድን በመቅረፅ ከሚያደርጉት ጎን ለጎን በግዥ አፈፃጸም ተግዳሮቶች፣ በልዩ ግዥ ፍላጎት መበራከት፣ በአቤቱታ እና ጥፋተኝነት ጉዳዮች መብዛት እና በግዥ አፈፃፀም ዙሪያ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶች፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች የጨረታ ሂደት ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶችና የመፍትሄ አቅጣጫዎቻቸዉ እንዲሁም በአጠቃላይ በግዥ ዙሪያ የሚታዩ የግብዓት ጥራት ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው እና ሌሎች የአሰራር ግድፈቶችን በመቅረፍ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡  ከምክክር መደረኩ በግዥ አፈፃጸምና አጠቃላይ በንብረት አስተዳደር ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቀነስ ዙሪያ ትልቅ አስተዋፅኦ ከሚኖረው ባሻገር በአገር ደረጃ ከ70% በላይ የሚሆነውን የመንግስት በጀት ውጤታማነትን ከማሳደግ አንፃርና የመንግስትን የግዥ አፈፃፀምና ንብረት አስተዳደርን ከብክነት ለማዳን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚደረግ ምክክር መድረክ በመሆኑ ባለሥልጣኑ ለሚያከናውነው የተቆጣጣሪነት ሚና አጋዥ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡

የመጀመሪያው ዙር በቢሾፍቱ ከተማ አዱላላ ሆቴል፣ ሁለተኛው ዙር ደግሞ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቦንጋ ከተማ ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከየካቲት 17-19 ቀን 2014 ዓ ም መከናወኑ የሚታወስ ሲሆን፤ይህ ሶስተኛ ዙር ምክክር መድረክ ደግሞ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በባህርዳር ከተማ አቫንቴ (ብሉ ናይል) ሆቴል የሚደረግ ምክክር በግዥ ላይ የሚደረግ ሌብነትን የማክሰም ዘመቻ አካል ነዉ። የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን በሶስተኛ ዙር የምክክር መድረክ እየተሳተፉ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተሳታፊዎች የግዥ ስርዓት ላይ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ገልፀው ከጊዜ ጊዜ እያከናወኗቸው የሚገኙትን የግዥ ስርዓቶች በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማስቻል ባለፈ የግዥ ስርዓታቸውን ተቆራርጠው መምራት መጀመራቸውን ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

ባለስልጣኑ ተቋማትን ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ በማለት የሚፈርጅበትን ግልፅ መስፈርት በማስቀመጥ መገምገም የሚኖርበት ሲሆን ከዚህ በፊት በተቋሙ የወጡ አዋጆች፣ ሰርኩላሮችና መመሪያዎች ተሻሽለው ቢቀርቡ የግዥ ስርዓቱን ውጤታማና ቀልጣፋ ያደርገዋል ብለዋል፡፡  የገበያ ዋጋ መዋዠቅና አቅርቦትን ከገበያ ማጣት ለዩኒቨርስቲዎች ተግዳሮት መሆኑን ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡ ለምክክር መድረኩ ውጤታማነት የዩኒቨርስቲዎች የግዥና ፋይናንስ እንዲሁም ኦዲት ዳይሬክትሮች መሳተፍ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡  በተጨማሪም ኦዲተር ጀኔራል፣ የመንግስት ግዥ አገልግሎትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በምክክር መድረኩ መሳተፍ እንዳለባቸው ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በሶስተኛ ዙር የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በግዥ አፈጻጸምና ንብርት አስተዳደር ዙሪያ በሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና በወቅታዊ የገበያ ሁኔታ ዙሪያ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አመራሮች በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ በተጋባዥ እንግዶች ማላትም ማቴዎስ ኢንሰርሙ(ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ልማት ፕሬዝዳንት ግዥ ለአካባቢና ለዘላቂ ልማት፣በተመስገን ወንድሙ(ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ትምህርት የግንባታ ግዥና ውል አስተዳደር የሚስተዋሉ ችግሮች በሚል ርዕስ ጥናቶች እንዲሁም የዘመናዊ የንብረት አስተዳደርና ነዳጅ አጠቃቀም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማቅረብ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡