The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በመንግስት ንብረት አወጋገድ ሥርዓት ላይ አዲስ መመሪያ ወጣ

ተቋማት በዓመት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ማስወገድ እንዲችሉ የሚፈቅድ መመሪያ መዘጋጀቱ ተገለፀ::

ተቋማት በዓመት እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ማስወገድ እንዲችሉ የሚፈቅድ መመሪያ መዘጋጀቱን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሐጂ ኢብሳ እንደገለፁት፤ ቀደም ሲል የነበረው መመሪያ በርካታ ክፍተት ስለነበሩበት ተቋማት ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ ዕቃዎች ማስወገድ ላይ ችግር ፈጥሮባቸው ቆይቷል።

አዲስ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ካልሆኑ በስተቀር ነባር ተቋማት በርካታ ንብረቶችን ያለ አገልግሎት አከማችተው እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ሐጂ፣ ግብና፣ ጤና፣ ገንዘብ፣ ንግድ፣ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ከተቋቋሙበት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በርካታ ንብረቶችን አጠራቅመው እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

አዲሱ መመሪያ ከዚህ በፊት በነጠላ እስከ አንድ ሺህ ብር በዓመት ውስጥ ደግሞ እስከ መቶ ሺህ ብር የሚያወጡ ንብረቶችን ተቋማት እንዲያስወግዱ ይፈቅድ እንደነበር አመልክተው፣ በተሻሻለው መመሪያ በነጠላ ዋጋ አምስት ሺህ በዓመት ደግሞ እስከ ግማሸ ሚሊየን ብር ማስወገድ እንዲችሉ ሥልጣን ይሰጣቸዋል ብለዋል።

የተሻሻለው መመሪያ ተከማችተው የሚገኙ ንብረቶችን በዘላቂነት ለማስወገድና ወደፊት ክምችት እንዳይኖር እንደሚያደርግ ጠቁመው፣ መመሪያው በገንዘብ ሚኒስቴር ተፈርሞ በ185 የፌዴራል ተቋማት መሠራጨቱን አስታውቀዋል።

እንደ ተሽከርካሪ፣ ማሽነሪና ቁርጥራጭ ብረቶች ያሉ ንብረቶችን በቀጥታ በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር እንደሚወገድ የገለፁት አቶ ሐጂ፣ አነስተኛ ዋጋ ያላቸውን ደግሞ ተቋማት በራሳቸው የሚያስወግዱበት ሥልጣን ይኖራቸዋል ማለታቸው ተዘግቧል።

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት