The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ከሚያዝያ 4-8 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄደውን የንብረት ምዝገባ ሳምንትን በማስመልከት ለተመረጡ መ/ቤቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ 31 ለሚሆኑ ለተመረጡ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች ከሚያዝያ 4-8 ቀን 2013 ዓ.ም የሚካሄደውን የንብረት ምዝገባ ሳምንትን በማስመልከት መጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጠ፡፡

ክቡር አቶ ሃጂ ኢብሳ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ስብሰባውን የከፈቱ ሲሆን፣ በመክፈቻው ንግግር ላይ እንደተናገሩት ከፍተኛ ወጪ የወጣባቸው የመንግስትና የህዝብ ሀብት በየቦታው ወዳድቆ በፀሀይና በዝናብ ምክንያት በመበላሸት ለብክነት እየተዳረጉ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህ እየባከኑ ያሉትን ንብረቶችን በመመዝገብ በሽያጭ ወደ ገንዘብ የሚቀየሩትን ለመቀየርና የሚወገዱትን ለማሰወገድ ከሚያዝያ 4-8 ቀን 2013ዓ.ም በሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች የሚካሄደውን የንብረት ምዝገባ ሳምንትን በሚመለከት ዐቢይ ኮሚቴ ሆነው ለተመረጡ መ/ቤቶች ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፐሮግራም በኤጀንሲው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ነጋሽ ቦንኬ የዋናው ዳይሬክተር አማካሪ አጭር ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ያለ አገልግሎት የተከማቹ የመንግስት ንብረቶች ምዝገባ ንቅናቄን በሚመለከት ስለንቅናቄው ዓላማ እና የሚጠበቅ ውጤት፣ያለ አገልለግሎት የተከማቹ ንብረቶችን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ በኤጀንሲው የተዘጋጀ አጭር የቪዲዮ ማሳያ፣ የቅድመ ምዝገባ ምዕራፍ ሥራዎች፣ በምዝገባ ምዕራፍ የሚከናወኑ ስራዎች፣ በድህረ ምዘገባ ምዕራፍ የሚከናወኑ ስራዎች እንዲሁም ሊገጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ዋና ዳይሬክተሩ ግዥን መለወጥ ማለት ሃገርን መለወጥ እንደሆነና ግዥ ማለት ንብረት ማለት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡አቶ ወልደአብ ደምሴ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በውይይቱ ላይ በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን ገልጸው፣ የንቅናቄው ዓላማ እነዚህን ጉዳዮች  ለመፍታት አቅም እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ከተሳታፊዎች ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ተጠይቀው መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት