The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ 35 ከሚሆኑ የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶችና የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ሥርዓትን ለማሻሻል የሚያግዝ የምክክር መድረክ የካቲት 25/2013ዓ.ም በገንዘብ ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ አካሄደ፡፡

ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመክፈቻውም ንግግር ላይ እንደተናገሩት የመንግስት ግዥን በዕቅድ ላይ በተመሰረተና ገንዘብ ሊያስገኝ የሚችለውን ከፍተኛ ጥቅም /Value for Money/ ማስገኘት በሚያስችል መልኩ መፈጸም እንዳለባቸው፣ እንዲሁም በዚህ መልኩ የሚገኝን የመንግስትና ህዝብ ሃብት የሆነውን ንብረቶች በአግባቡ ይዘው ሊያስተዳድሩና አገልግሎት ላይ ሊያውሉ እንደሚገባ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ሲያልፍም ለበለጠ ጉዳት ከመዳረጋቸው በፊት፣ በሰውና በአከባቢ ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው አስቀድሞ መንግስት በዘረጋው የአወጋገድ ሥርዓት መሠረት ሊያስወግዱ እንደሚገባ በመንግስት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 እና በአፈጻጸም መመሪያዎች ተደንግጎ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በአገራችን የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ትግበራ ተጠናቆ ቀጣዩ*ኢትዮጵያ አፍርካዊት የብልጽግና ተምሳሌት” በሚል መሪ ቃል የሚታወቀው ከ2013ዓ.ም እስከ 2022ዓ.ም የሚቆየው የ10 ዓመት ዕቅድ እና የዚሁ አካል የሆነው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በመተግበር ላይ እንደሚገኝ፣ የተጠናቀቀውም ሆነ ወደ ትገበራ በመግባት ላይ የሚገኘው የልማትና የእድገት ዕቅዶች ማዕከል ያደረጉት አረንጓዴ ኢኮኖሚን መሆኑን፣ በዚህም ረገድ በተጠናቀቀው የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ወቅት አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚያግዙ በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በመሠረተ ልማት ዘርፎች፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በትራንስፖርትና በሌሎችም መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፎች መልካም የሚባሉ ጅምሮችና ውጤቶች መመዝገባቸውን እና እነዚህ መልካም ጅምሮች የታዩባቸውን ድክመቶች በማረም ለቀጣዩ ዕቅድ ትግበራ እንደ መንደርደሪያ የሚያለግሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህ የምክክር መድረክ ላይ ከተሳታፊዎች ገንቢ የሆኑ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ተጠይቀው መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡

በፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት