The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግሥት ግዥና ንብረት ታሪካዊ አመጣጥ

የመንግሥት ግዥ ከ1935 ዓ.ም ጀምሮ አንድ ጊዜ በተማከለ በሌላ ጊዜ ደግሞ ባልተማከለ መንገድ ሲፈፀም እንደነበር ቀደምት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይኸዉም፡-
ከ1935ዓ.ም እስከ 1950 ዓ.ም የሁሉም መንግሥት መ/ቤቶች ግዥ ተጠቃሎ በገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት ይከናወን እንደነበርና አፈፃፀሙ ከፍተኛ መዘግየትና አልፎ አልፎም የአገልግሎት መቋረጥ ይታይበት ስለነበር ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን አሠራር ሙሉ ለሙሉ እንዲቋረጥ መደረጉ፡፡
ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት ንብረት ሚ/ር /Ministry of stores and supplies/ የሚባል እራሱን የቻለ መ/ቤት እንዲመሰረት ተደርጎ የመንግሥት መ/ቤቶች ግዥ ተጠቃሎ ይከናወን እንደነበርና የዚህ ሚ/ር መ/ቤት አመሰራረት በቂ ጥናት ያልተደረገበትና በችኮላ የተቋቋመ በመሆኑ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀምን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ችግሩን ስላባባሰው ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ፈርሶ የገንዘብ ሚኒስቴርና የዋናው ኦዲተር መ/ቤት ሁሉም አስፈፃሚ የመንግስት መ/ቤቶች የሚመሩበትን የግዥ መመሪያ በጋራ በማዘጋጀት ከብር 150,000,00 በላይ የሆኑትን የመንግሥት መ/ቤቶች ግዥ አፈፃፀም የሚመረምር ማእከላዊ የግዥ ኮሚቴ እንዲመሰረት ተደርጓል፡፡ ይሁን አንጂ በዚህም አሠራር የመንግሥት ግዥ ችግሮች ከመወገድ ይልቅ በመባባሳቸው መ/ቤቶች በማዕከላዊው የግዥ ኮሚቴው ቁጥጥር የሚደረግበትን የገንዘብ ጣሪያ ለመሸሽ ሲሉ ግዥዎቻቸውን እየከፋፈሉ በቁጥቁጥ መግዛት ስለጀመሩ አሠራሩ ከታሰበው ዓላማ ውጭ የጥቅል ግዥ በተበታተነ ግዥ እንዲተካና በአስቸኳይነት ሽፋን አብዛኞቹ ግዥዎች የግልፅ ጨረታ ሂደትን ባልተከተለ መንገድ እንዲፈጸሙ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ በመቻሉ፡፡
ለተፈጠረው የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም ችግር መፍትሄ ለመስጠት በ1969 ዓ.ም የመንግሥት ዕቃ ግዥና አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መምሪያ በሚል መጠሪያ በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር አንድ የሥራ ክፍል ተዋቅሮ እስከ 1973 ዓ.ም ድረስ መጠናቸው እስከ ብር 150,000,00 ድረስ ያሉ ግዥዎችን አስፈፃሚ መ/ቤቶች በራሳቸው እንዲፈፅሙ የግዥ ስልጣን (ውክልና) በመሥጠትና ከዚያ በላይ የሆኑ ግዥዎችን ግን ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሌሎች መ/ቤቶች ተውጣጥቶ በተቋቋመ ኮሚቴ አማካኝነት እየተመረመሩ እንዲፈፀሙ ሲደረግ ቆይቷል፡፡በዚህ አሠራር ችግሮቹ በተወሰነ ደረጃ የተቃለሉ ቢሆንም ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ ለመስጠት የመንግሥት ግዥ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ የሚመራበት ሁኔታ ተጠንቶ በወጣው የ1973ቱ የፋይናንስ ደንብ ቀደም ሲል ለመንግሥት መ/ቤቶቹ ተሰጥቶ በነበረበት ወቅት የግዥ ስልጣን ውክልና ከብር 150,000,00 ወደ ብር 250,000,00 ከፍ እንዲል ተደጓል፡፡
በ1973 የፋይናንስ ደንብ መሠረት በመንግሥት እቃ ግዥና አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መምሪያ ሥር የማዕከላዊ ጨረታ ውሳኔ መርማሪ ኮሚቴ ጽ/ቤት የሚባል የሥራ ክፍል ተመስርቶ ከብር 250,000,00 በላይ የሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ግዥዎችን አስቀድሞ የጨረታ ዶክመንቶችን እየመረመረ ግዥውን ሲፈቅድ ከቆየ በኋላ በመቀጠል በ1986 የገንዘብ ሚ/ር መዋቅር በአዲስ መልክ ሲጠና የመንግሥት ዕቃ ግዥና አጠቃቀም መቆጣጠሪያ መምሪያ እንዲታጠፍ ተደርጎ በጠቅላላው 3 የሰው ሃይል ያለው የግዥ ዩኒት በመባል በምክትል ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ሥር ተቋቁሞ እስከ 1991ዓ.ም ድረስ ግዥው የሚመለከታቸው የመንግሥት መ/ቤቶች ተወካዮች በአባልነት በሚሳተፉበት የማዕከላዊ ጨረታ ውሳኔ መርማሪ ኮሚቴ አማካኝነት እተገመገመ ተቀባይነት ሲያገኝ ግዥው ሲፈፀም ቆይቷል፡፡
ከመጋቢት 1991ዓ.ም ጀምሮ በመምሪያ ደረጃ ተቋቁሞ የመንግሥት ግዥ መመሪያ ቁጥር 1/1991 ስራ ላይ እንዲውል የተደረገ ሲሆን የአስፈፃሚ መ/ቤቶች የግዥ ስልጣን ውክልናም በዚህ መመሪያ መሠረት ሁለት ቦታ ተከፍሎ ለአገር ውስጥ ግዥ እስከ ብር 500,000 ለአለም አቀፍ ግዥ ደግሞ እስከ ብር 2,000,000 ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡
በየጊዜው የሚደረገውን ማሻሻያ ተከትሎ በ1993ዓ.ም የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር መምሪያ በስሩ ሶስት ቡድኖች ማለትም ፡-
1.የጨረታ ምርመራና ግምገማ ቡድን፣
2.የግዥ ጥናትና መረጃ ማደራጃ ቡድን፣
3.የመንግስት ንብረት አስተዳደር ቡድን፣
እንዲኖሩት በማድረግና አዲስ አደረጃጀት በመፍጠር በ1997 ዓ.ም የመንግሥት ግዥ ኤጀንሲ በአዋጅ እስኪቋቋም ድረስ ከላይ በተጠቀሰው አደረጃጀት በመጋቢት ወር 1991ዓ.ም በወጣው የግዥ መመሪያ መሠረት መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ከሞላ ጎደል ሲወጣ ቆይቷል፡፡
የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር መምሪያ በቀድሞው በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ሥር የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻያ ጥናት በግምባር ቀደምትነት እንዲካሄድባቸው ከተመረጡት መምሪያዎች ውስጥ ንብረትን ሳይጨምር ግዥውን በተመለከተ ሥራ እንደመሆኑ መጠን ከ1995ዓ.ም እስከ 1996ዓ.ም ድረስ በመምሪያው ይሰጡ የነበሩትን አገልግሎቶች ችግር በአግባቡ የፈተሸና ለኤጀንሲው መወለድ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተ የማሻሻያ ጥናት ለማካሄድ ተችሎዋል፡፡  
በመሆኑም በማሻሻያ ጥናቱ መሠረት በ1997 ዓ.ም የመንግሥት ግዥን ሙሉ ለሙሉ ለግዥ ፈፃሚ አካላት በመስጠትና ወደ አልተማከለ አሠራር በመቀየር ለበርካታ አመታት ሲንከባለሉ ለቆዩት አብዛኞቹ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀም ችግሮች መፍትሄ የሰጠና በተበታተነ መልክ ሲሰራባቸው የቆዩትን የግዥ ደንብና መመሪያዎችን በማጠቃለልና በማሻሻል፣የመንግሥት ግዥ አዋጅ ቁጥር 430/97 እና የአፈፃፀም መመሪያው ተሻሽሎ እንዲወጣ የተደረገ ሲሆን በዚሁ አዋጅ ተጠሪነቱ ለቀድሞ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የሆነ የመንግሥት ግዥ ተቆጣጣሪ ኤጀንሲም እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
በመቀጠልም ለመንግስት ንብረት ልዩ ትኩረት ሊሠጥ እንደሚገባ በተሠጠው አስተያየት የዳሰሳ ጥናት ውጤት መሠረት የመንግሥት ግዥና ንብረትን አንድ ላይ እንደገና በማዋሀድ በአዋጅ ቁጥር 649/2001 የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በጰጉሜ 4 ቀን 2001ዓ.ም ተቋቋሞ የመንግሥት ግዥ አፈፃፀምንና የንብረት አስተዳደሩን እየመራ ይገኛል፡፡