The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ኤጀንሲው በ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ገመገመ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀምን በተመለከተ ከመላው የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር ጥር 15 ቀን 2011 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልገሎት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የስብሰባው ዓላማ በዚህ በ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የታቀዱ ተግባራት፣የተከናወኑ ተግባራት፣ያልተከናወኑ ተግባራት እና በዕቅድ ተይዘው ያልተከናወኑበት ምክንያት ለመወያየትና በቀጣይ መሰረት ለማስቀመጥ መሆኑን ለውይይቱ ታዳሚዎች ገልጸዋል፡፡በመቀጠልም ወ/ሮ አበባ ዓለማየሁ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የኤጀንሲውን የ2ዐ11 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ አመት የዕቅድ አፈፃፀምን ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን፣ ኤጀንሲው በመጀመሪያው ግማሽ አመት ለማከናወን ያቀደቸውን ማለትም የፈፃሚ ዝግጅትን፣ የተገልጋዮችና ባለድርሻዎችን ዕርካታ ማሳደግ፣የውስጥና የውጭ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት መፍታት፣ የሀብት አጠቃቀምና ውጤታማነት ማጎልበት፣ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ሪፎርም ሥራዎችን ማጠናከር፣ የመንግሥት ግዥ አስተዳደር አፈፃፀምን ማሻሻል፣ ከመ/ቤቶች የሚቀርቡ ዓመታዊ የግዥ እቅዶች በትክክለኛው የጥራት ደረጃ ተዘጋጅተው መቅረባቸውን በመፈተሽ ለመ/ቤቶች ግብረ መልስ መስጠት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም የግዥ አፈጻጸም እና ንብረት አወጋገድ አቤቱታዎች እና የጥፋተኝነት ሪፖርቶች ውሳኔ አሰጣጥ ማሻሻል፣ የዘርፈ ብዙ ጉዳዩዮችን በማካተት ተሣታፊነትና ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ የለውጥ ሥራዎችን ውጤታማነት ማሳደግ፣ የሰው ሀብት አቅም ማሳደግ፣ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምንና የሥራ አካባቢ ምቹነት ማሳደግ እና በአጠቃላይ በግማሽ በጀት ዓመቱ የተገኙ ዋና ዋና ውጤቶች፣የክትትልና  ግምገማ አፈፃፀም፣ያጋጠሙ ችግሮች፣ የመፍትሔ እንዲሁም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን በሚመለከት ሰፊ ማብራሪያ አድርገዋል፡፡

በመቀጠልም ዳይሬክተሯ የተዘጋጀው ዕቅድ ውጤት ተኮር ሥርዓት መሠረት ወደ ዳይሬክቶሬቶች ከዚያም ወደ ሠራተኛው የወረደ ሲሆን በኤጀንሲው በተደራጁ 17 የ1ለ5 የካይዘንና የለውጥ ሠራዊት ቡድኖች አማካይነት ሳምንታዊ የሥራ ዕቅድ እየተዘጋጀ አፈፃፀሙን እየተገመገመ ዕቅዱ እንዲተገበር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ዳይሬክተሯ የ2011 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በዝግጅት ምዕራፍ የተከናወኑት እና ወደ ትግበራ ምዕራፍ በመሸጋገር የተሰሩትን ስራዎችን በማካተት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች እና አስተያቶች የተነሱ ሲሆን በተነሱትም ጥያቄዎች ላይ የኤጀንሲው አመራሮች በቂ ምላሽ እና ማብራሪያ  በመስጠት የማጠቃለያ ንግግር በማድረግ የጋራ ግንዛቤ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ ለግማሽ ቀን በቆየው የዉይይት መድረክ ላይ የኤጀንሲዉ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብግንኙነትናኮሚዩኒኬሽንዳይሬክቶሬት