The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ሙስና በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደረሰውን ተፅዕኖ በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከፌደራል ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በመተባበር ሙስና በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ እና መወሰድ ስለሚገባቸው የመፍትሔ እርምጃዎችን በሚመለከት ለኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ህዳር 27/2011 ዓ.ም. በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት  የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዉስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጠ፡፡

አቶ ፍሬሁን መለስ በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን የፊት ለፊት ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ ሥልጠናውን የሰጡ  ሲሆን፣ ሙስና ምንድነው ከሚለው ተነስተው ሙስና ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመስራት ይልቅ ስልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ ህግና ሥርዓትን በመጣስ የመንግስትና የህዝብ ሃብትና ንብረትን መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበር እንዲሁም በጉቦ፣ በዝምድና፣ በትውውቅ በጐስኝነት፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በኃይማኖት ትሥሥር በመመርኮዝ ፍትህን አያዛቡ የግል ጥቅምን ማካበትና ሌላውን ወገን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥቀም ወይም መጉዳት መሆኑን ስረድተዋል፡፡በመቀጠልም አሰልጣኙ የሙስና ወንጀል ልዩ ባህሪያትን ሲገልጹ የአፈፃፀሙ ሂደት እና ሥልት፣ለጉዳዩ ባለቤት ነኝ ባይ አለመኖር፣ የፈፃሚዎቹ ማንነት እና ምርመራውን ለማኮላሸት እና መርማሪውንም ሆነ ከምርመራው ጋር ግንኙነት ያላቸውን ግለሰቦች ለማጥቃት መቻላቸውና በሕዝቡ ዘንድ እንደ ነውር አለመታየቱ እና ሙስናን በመዋጋት ተግባር ላይ የተሰማሩትን ሰዎች ማሸማቀቁ መሆኑን፣ እንዲሁም የሙስና ዓይነቶች ዝቅተኛ፣ከፍተኛ እና ፖለቲካዊ ሙስና መሆናቸውንና መገለጫቸውም ጉቦ፣ ምዝበራ፣ ማጭበርበር፣ በዝምድና እና በወዳጅነት መሥራት/አድሎ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡በመጨረሻም ሙስና ዓለም አቀፍ ወንጀል እንደሆነና በመንግሥት መ/ቤትና  ሕዝቡ ውስጥ በተወሸቁ ዘራፊዎች ትብብር የሚፈጸመው ይህ አስከፊ ወንጀል ዜጎችን እርቃን የሚያስቀር፣ ጥቂቶችን የሚያበለፅግ፣የመንግሥትን ተዓማኒነት የሚሸረሽርና ሕዝብን የሚያማቅቅ አደገኛ ችግር እነደሆነና ከዚህ አንፃር በአገራችንም ዓይነቱና መጠኑ ቢለያይም ወንጀሉን በጥብቅ መታገል ካልተጀመረ ከፊት ለፊት የተደቀነው አደጋ የከፋ መሆኑን አስረድተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለአንድ ቀን በቆየው በሙስና ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ የኤጀንሲው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት