The FDRE Public Procurement & Property Administration Agency

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ

ከተመረጡ የመንግስት መ/ቤቶች ጋር በግዥና ንብረት ኦዲት ግኝቶች ዙሪያ የምክክር መድረክ ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በዋና ዋና የኦዲት ግኝቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከተመረጡ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች ጋር በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አዳራሽ ከመስከረም 9–10/2011 ዓ.ም. የጋራ የምክክር መድረክ አካሄደ፡፡ክብርት ወ/ሮ ማርታ ሉዊጂ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በምክክር መድረኩ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የመድረኩ ዓላማ በመንግስት ግዥና ንብረት አሰተዳደር ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ዉይይት በማድረግ የሚፈቱበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ እንዲያስችል የተዘጋጀ የምክክር መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ዋና ዳይሬክተሯ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ቀጣይ የሆነ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፉን ከማሻሻል ጀምሮ የአዋጁ ማሰፈጸሚያ መመሪያዎችንና ማኑዋሎችን የማዘጋጀት፣ በወረዳ መዋቅር ካላቸው የስራ ባህሪ አጣጥመው ሊጠቀሙት የሚችሉትን የግዥ መመሪያዎችን የማዘጋጀት፣ የሙያ ስልጠናዎችን የመስጠት፣ የግዥና ንብረት አሰተዳደር ስራዎችን በዋና ዋና መለኪያዎች የመመዘን፣ የኤሌክትሮኒከ ግዥ ዘዴን ተግባራዊ በማድረግ በተለይም ግልጸኝነትንና የመረጃ ተደራሽነትን በማስፋት ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር በኤጀንሲው የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን ትኩረት በመስጠት በተለይም በዘንድሮው በጀት ዓመት በሙከራ ትግበራ በመጀመር በቀጣይም በሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶች ለማስፋት ታስቦ የተጀመረውን ኢ-ፕሮክዩርመት ሁላችንም ቅድሚያ ትኩረት ሰጥተን ልናሳካ ይገባል ብለዋል፡፡በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሯ አሁን ያለንበት ወቅት ከምን ጊዜውም በላይ በአገራችን የተጀመረውን የልማትና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት ቀጣይነት ለማረጋገጥ የምንተጋበት፣ በተሰማራንበት የስራ መስክ የሕዝብ አገልጋይነታችንና ወገንነታችንን የምናጠናክርበት በተለይም ከተልዕኮአችን አንጻር በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር አፈጻጸም ዙሪያ የሚስተዋሉ የመልካም አሰተዳደር እጦት መገለጫ የሚሆኑና ለኪራይ ሰብሳቢነትና ብልሹ አሰራር በር የሚከፍቱ አሰራሮችን በመዝጋት በምትኩ ተገልጋይን ማዕከል ያደረገ አሠራርን እና መልካ አስተዳደርን በማስፈን፣ በሀገር አቀፍ የተጀመረውን የለውጥ አመራር እና የመደመር ጉዞ ከዳር ለማድረስ በጋራ በመመካከርና በመወያየት የሚያጋጠሙንን ችግሮች ለመፍታ አንዱ ከሌላው ተሞከሮ በመውሰድ የመንግስትን ውስን ሀብት በአገባቡ በመጠቀም ልማታችንን ለማፋጠን መረባረብ እንደሚጠበቅብን ገልጸዋል፡፡አቶ ነጋሽ ቦንኬ በመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ስልጠና የሰጡ ሲሆን ሰለ አቤቱታ ማጣራት፣ አቀራረቡና ሰለስነ-ሥርዓቱ፣ በግዥ ፈጻሚው መ/ቤት ሰለሚካሄድ የአቤቱታ ማጣራት ሂደት፣ ስለ ግዥ አፈጻጸምና ንብረት አወጋገድ አቤቱታ አጣሪና ውሳኔ ሰጪ ቦርድ፣ አቤቱታ ሰለሚቀርብባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣አቤቱታ ማቅረብ ስለማይቻልባችወ ጉዳዮች፣ የጥፋተኝነት ሪፖርት ስለማይቀርብባቸው ሁኔታዎች የጥፋተኝነት ሪፖርት ሰለሚቀርብባቸው ጉዳዮች ላይ እና ሰለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት አጠቃላይ ገጽታ እና በአፈጻጸም ሰለታዩ የአሰራር ችግሮች በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡

በመቀጠልም አቶ ነጋሽ በ2010 ዓ.ም በፌደራል የግዥ እና ንብረት ኦዲትና ክትትል ዳይሬክቶሬት በተደረገ የግዥ ኦዲት ወቅት ሰለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣በ2010 ዓ.ም በዋና ኦዲተር ኦዲት ወቅት በግዢ፣ በንብረትና በተሸከርካሪ ስምሪት ላይ ሰለተገኙ ዋና ዋና ግኝቶች፣ በ2010 ዓ.ም በመንግስት ግዥና ንብረት ኦዲትና ክትትል የግዢ ኦዲት ተደርገው የኦዲት ግኝት ስለታየባቸው መ/ቤቶችና ግኝቶቻቸው ደጋፊ ሰነዶች፣ በ2011 ዓ.ም ኦዲት ወቅት ግኝቶችን በመቀነስ የተሻለ የግዢ፣የንብረትና የተሽከርካሪ ስምሪት አፈፃፀም እንዲኖር የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ስለማድረግ፣ በግዢ፣ በንብረትና በተሽከርካሪ ስምሪት ስርአቱ ውስጥ ያሉ በኦዲቱ የተለዩትን ግኝቶችና በምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሐሳቦችን በማካተት የአቅም ግንባታውን ስራ የበለጠ ተደራሽ ሰለ ለማድረግ እና የኦዲት ግኝቶችን በሪፖርት ላይ በተገለፀው ጊዜ እርምት እርምጃ ወስዶ በወቅቱ ያለማሳወቅ ምክንያትን ለመለየትና ለወደፊቱ የመፍትሄ አቅጣጫ ስለማስቀመጥ ገልጸዋል፡፡

አቶ ይገዙ ዳባ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ስልጠና የሰጡ ሲሆን አገልግሎቱ ስለፈጸማቸዉ ግዥዎች፣ ሰለውል አስተዳደር ተግባራት አፈፃፀም፣ስለአጋጠሙ ችግሮች፣ ችግሮችን ከመፍታት አንፃር የተuማት ሚና፣በአጠቃላይ በ2010 በጀት ዓመት የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት% ያጋጠሙ ችግሮች እና ችግሮችን በመፍታት ረገድ የኤጀንሲው፤ አገልግሎቱና ተጠቃሚ መ/ቤቶች ሚና በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ አሰተያየቶች የተሰጡ ሲሆን ጥያቄዎችም ተነስተው ለጥያቄዎቹም መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለሁለት ቀን በቆየው በዚህ የምክክር መድረክ ስብሰባ ላይ 100 የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት