The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የተቆጣጣሪነት ሚና ካላቸው መ/ቤቶች ለተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በመንግሥት ግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ሥልጠና ተሰጠ

የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ ዋና ኦዲተር እና የፍትህ አካላት በመንግሥት ግዥ  አፈጻጸም ዙሪያ ከታህሳስ 24—26 ቀን 2010 ዓ.ም. በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒሰቴር የስብሰባ አዳራሽ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡ አቶ ታደሰ ከበደ በመንግሥት ግዥ አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን ስለመንግሥት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ ዓላማና መርሆዎች፣ የመንግሥት ግዥ ሰለሚመራባቸው የህግ ማዕቀፎች፣ ሰለመንግስት ግዥ ትርጓሜ፣ ሰለመንግስት ግዥ ታሪካዊ አመጣጥ፣ ልዩ ባህሪያትና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች፣ ስለመንግስት ግዥ ዓይነቶችና ሂደት እንዲሁም የመንግሰት ግዥ ስለሚመራባቸው ሕጋዊ ሠነዶች በዝርዝር ገላጻ አድርገዋል፡፡

አቶ ገበያው ይታይህ በመንግሥት ግዥ አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ከፍተኛ ባለሙያ ከግዥ ዕቅድ በመነሳት ሰለግዥ ዕቅድ አሰፈላጊነትና ጥቅም፣ ሰለ ግዥ ዑደትና የግዥ ዘዴዎች ስለሆኑት ገልጽ ጨረታ፣የመወዳደሪያ ሃሰብ መጠየቂያ፣ የሁለት ደረጃ ጨረታ፣ ውስን ጨረታ፣ ዋጋ ማቅረቢያ፣ አንድ አቅራቢ እና በማዕቀፍ ስምምነት ስለሚፈጸም ግዥ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ወ/ሮ እፀገነት ቢሻው በግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ሰለአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት አጠቃላይ ገጽታ፣ ሥነ—ሥርዓቱ ሰለሚመራባቸው ህጎች፣ ሰለተሳታፊ ባለድርሻ አካላት፣ ሰለአቤቱታ ማጣራት እና ስለ ጥፋተኝነት ሪፖርት  ትርጉም፣ በአፈጻጸም ወቅት ስለምያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው እንዲሁም በመ/ቤቶችና በአቅራቢዎቸ ስለሚታዩ ግድፈቶች ሰፋ ያለ መብራሪያ ሰጥተዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ለሶስት ቀን በቆየው የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው  አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ላይ 60 የሚሆኑ የየመ/ቤቶቹ ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት