The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የትምህርት፣ የሥራ ልምድ እና የሙያ ማስራጃዎች የማጣራት ሥራን አስመልክቶ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ

በፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ለኤጀንሲው ሠራተኞች በፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የቀረቡ የትምህርት፣ የሥራ ልምድ እና የሙያ ማስራጃዎች  የማጣራት ሥራን አስመልክቶ በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የስብሰባ አዳራሽ ጥቅምት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. የግማሽ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጠ፡፡

አቶ መስፍን መኮንን በኤጀንሲው የሰው ሀብት ሥራ አመራርና ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በፌዴራል  መንግሥት  ሠራተኞች የቀረቡ የትምህርት፣ የሥራ  ልምድ  እና የሙያ ማስራጃዎች የማጣራት ሥራን አስመልክቶ በቀረበው ጽሁፍ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫውን የሰጡ ሲሆን፣ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት እና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ በርካታ ቀደም ሲል ያልነበሩ  ውስብስብ  ህጋዊ ሳይሆኑ ህጋዊነትን ተላብሰው የሚከናወኑ ተግባራት መከሰታቸው እንደማይቀር እና ይህም አሰራር ሃይ ካልተባለ በሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ህጋዊ አሰራሮች ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡፡
በመቀጠልም ዳይሬክተሩ የውይይቱ ዓላማው ህጋዊ አሰራርን አጠናክሮ ማስቀጠል፣ የተጠያቂነት አሰራርን ማስፈን፣ ቀደም ሲል የተፈፀሙ ህገ-ወጥ አሰራሮችን ማረምና ማስተካከል እና በሒደቱ ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት ሠራተኞች እንዲታረሙ እድል ለመስጠት እና በተሰጠው ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ፍቃደኛ ያልሆኑትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡፡

ስለመነሻ ሆኔታዎችም ሲያስረዱ በሀገሪቱ እየተመዘገበ በሚገኘው የኢኮኖሚ እድገት የሲቪል ስርቪስ ሠራተኞች ድርሻ ከፍተኛውን ቦታ የሚይዝ ሲሆን፣ ነገር ግን አብዛኛው የመንግስት ሠራተኛ ህጋዊ አሰራርን የሚከተል ቢሆንም ቁጥራቸው ቀላላ የማይባሉ የመንግስት ሠራተኞች ሀሰተኛ የትምህርት ፣የሥራ ልምድና የሙያ ማስረጃዎችን በማስያዝ በቋሚ ሠራተኝነት ተቀጥረው ሲሰሩ እንደተገኙ በክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች በተደረገው የማጣራት ሥራ መረጋገጡንም ገልጸዋል፡፡በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ለግማሽ ቀን በቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫ  ውይይት ላይ የኤጀንሲው ሃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

መ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት