The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ኤጀንሲዉ ከመላዉ ሠራተኞች ጋር ውይይት አካሄደ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመላው የኤጀንሲው ኃላፊዎች እና ሠራተኞች ጋር በ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም እና በ2010 ዕቅድን በተመለከተ ሃምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት  ኤጀንሲው በ2009 በጀት ዓመት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየ መሆኑና በበጀት ዓመቱ የተከናወኑትን አበይት አፈጻጸሞችን ገምግሞ አመርቂ ዉጤት ማስመዝገቡንና እና ዝቅተኛ አፈጻጸሞችን በመለየት ከመላው የኤጀንሲው  ሰራተኞች ጋር በጋራ በመወያየት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የተመዘገቡትን ዝቅተኛ አፈጻጸሞች እና ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ቁልፍ መፍትሄ ነው ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የ2010 በጀት ዓመት ዕቅዳችንን በጋራ ማቀዳችንና ለምናከናውነውን ስራ በግልፅና በቆራጥነት እንድንሰራና ወጥ የሆነ የጋራ አመለካከት እንዲኖረን ያደርጋል ብለዋል፡፡

በመቀጠልም በኤጀንሲው ስር የሚገኙ ዳይሬክቶሬቶች የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸማቸውን በአራቱ ዕይታዎች ማለትም ከተገልጋይ፣ ከፋይናንስ፣ ከውስጥ አሠራር፣ ከመማማርና ዕድገት ዕይታዎች አንጻር ዕቅድና አፈፃፀማቸውን በማነጻጸር  ገለፃ  አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም ያጋጠማቸውን አንኳር አንኳር የሆኑ ችግሮች፣ ስለተወሰዱ የማስተካከያ እርምቶች እና የወደፊት አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፊ ገለፃና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ዳይሬከቶሬቶቹ አክለውም የ2010 ዕቅዳቸውን ለተሳታፊዎች አቅርበው ሀሳብና አሰተያየት እንዲሰጥበት ተደርጓል፡፡

በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ ላይ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተዉ በተነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ የሚመለከታቸው ዳይሬክተሮች መልስ እንዲሰጡበት ከተደረገ በኋላ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር የማጠቃለያ ንግግር አድርገው የጋራ ግንዛቤ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡ለአንድ ቀን በቆየሁ የዉይይት መድረክ ላይ 110 የሚሆኑ የኤጀንሲዉ ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የመ.ግ.ን.አ.ኤ. ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት