The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

ከፌዴራል፣ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ የግዥ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከክልልና ከፌዴራል መንግስት ለተውጣጡ ለግዥ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ከሰኔ 5-9/2009 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ሪፍት ቫሊ ሆቴል ስልጠና ሰጠ፡፡
አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ተ/ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የስልጠናው ዋና ዓላማ በግዥ ላይ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት የእርስ በርስ ልምድ ልውውጥ በማድረግ የሙያ ክህሎታችንን ለማዳበርና የአቅም ውስንነትና ክፍተታችንን ለመሙላት በእጅጉ ያግዘናል በማለት ስልጠናውን በይፋ ከፍተዋል፡፡
በመቀጠልም በዘርፉ ልምድ ያላቸው የኤጀንሲው የግዥ ባለሙያዎች በተለያዩ የግዥ ጉዳዮች ላይ ስልጠና የሰጡ ሲሆን፣ በመጀመሪያው ቀን የተሰጠው ስልጠና ስለ ቁልፍ ውጤታማ የግዥ አመለካቾች (Key Performance Indicators of Procurement) ላይ ሰፋ ያለ ገለፃ ተደርጎ በጉዳዩ ላይም ለሙከራ ተመርጠው ተግባራዊ ሲያደርጉ የቆዩ አራት ክልሎች ልምዳቸውን በማካፈል አጠቃላይ ግንዛቤ ተሰጥቷል፡፡ በቀሩት አራት ቀናቶችም የመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፣ የግዥ እቅድና የግዥ ዘዴዎች፣ የጨረታ ሰነድ ይዘት፣ ዝግጅትና ግምገማ ሂደትና የአቤቱታና የጥፋተኝነት ሪፖርት ማጣራት ሂደት ላይ   የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በስልጠናው መጨረሻም የኤጀንሲው ተ/ዋና ዳይሬክተር አቶ ጆንሴ ገደፋ ስልጠናውን አሰመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው  ስኬታማ እንደነበርና በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው ሁሉም አካል ለመንግስት ገንዘብ ተመጣጣኝ ዋጋ ማስገኘት እንዲችል የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
በመጨረሻም የስልጠናው ተሳታፊዎች ሀሳብና አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ በተነሱት ጉዳዮች ዙሪያ ተ/ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ አድርገው የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ ስልጠናው ተጠናቋል፡፡
የመ.ግ.ን.አ.ኤ. ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት