The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በከይዘን አተገባበር ዙሪያ ውይይት አካሄደ

የፌዴራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጥምረት በከይዘን አተገባበር ዙሪያ  ግንቦት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡
በዕለቱ የለውጥ ትግበራ ዕቅድ ዝግጅትና ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አድማሱ ማሞ አጠቃላይ የኤጀንሲውን የከልቡ (ከይዘን ልማት ቡድን) የ5ቱ ማዎችና የብክነት ነባራዊ ሁኔታ ዳሰሳ የሚገኝበት ደረጃና የተጣሉትን ግቦች በከይዘን የትግበራ ዕወጃ ያቀረቡ ሲሆን፣ የከይዘን 5ቱ ማዎች ማለትም ማጣራት፣ ማስቀመጥ፣ ማጽዳት፣ ማላመድና ማዝለቅን በተመለከተ ለተሳታፊዎች አብራርተዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ መኮንን ያኢ የኢትዮጵያ የከይዘን ኢንስቲቲዩት ዋና ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር ከይዘንን መተግበር ያለብን ይተግበር ስለተባለ ብቻ ሳይሆን ሀገርንና ህብረተሰቡን ለመለወጥ ያለውን ጉልህ ሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከይዘንን ተግብረው ስኬታማ የሆኑ ሀገራት ተሞክሮ በመጥቀስ ሁሉም ሰው በመ/ቤት ደረጃም ብቻ ሳይሆን በግላችን ከቤታችን ጀምሮ እንኳ ብንተገብረው ውጤታማ ያደርገናል በማለት ሁሉም አካል  ለከይዘን ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም አቶ ጆንሴ ገደፋ የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም የኤጀንሲው ሰራተኞች ከይዘን የለውጥ መሳሪያ እንጂ ተጨማሪ ሸክም መስሎ እንዳይታየውና በቆራጥ መንፈስ የታቀደውን የከይዘን ዕቅድ መተግበር አለበት ብለዋል፡፡ ከይዘንን በትክክል ብንጠቀምበት መ/ቤቱን ከመለወጥ አልፎ ሃገርን የሚለውጥ መሳሪያ እንደሆነ ገልጸው፣ ትልቁ ጉዳይ የአመለካከት ጉዳይ በመሆኑ የኤጀንሲው ከፍተኛ አመራሮችም ከይዘንን ለመተግበር ያላቸው ቁርጠኝነት ከፍተኛ መሆኑን አሰታውቀዋል፡፡
ከይዘን የሚያስገኘውን ጥቅም በትክክል በማጤን ለትግበራው ሁሉም አካል የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ውይይቱም እንደተጠናቀቀ የኤጀንሲው ሰራተኞችና ሃላፊዎች ከይዘንን በይፋ ለመተግበር ያላቸውን ቁርጠኝነትና ፍላጎት ለመግለጽ የጋራ የጽዳት ዘመቻ በማካሄድ የዕለቱን የውይይትና የጽዳት ፕሮግራም አጠናቀዋል፡፡    
ከመ.ግ.ን.አ.ኤ. የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት