The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

41ኛው ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) በሚመለከት ስብሰባ ተካሄደ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎትና ከኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ጋር በመተባበር 41ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 8) በሚመለከት የካቲት 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ ውይይት አካሄደ፡፡

አቶ አክሊሉ ገብረስላሴ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሚኒሰትሩ ጽ/ቤት ኃላፊና አማካሪ በመክፈቻው ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት የሴቶች የረጅም ጊዜ የነጻነት ትግል ውጤት የሆነው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ106ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ41ኛ ጊዜ በተለያዩ ትምህርት ሰጪ ፕሮግራሞች ‹‹የሴቶች የቁጠባ ባህል ማደግ ለህዳሴያችን መሰረት ነዉ!›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ መሆኑንና በአደጉት እና በታዳጊ ሀገሮች ሰለዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ታሪካዊ አመጣጥና አከባበር በዝርዝር ገልጸዋል፡፡

ወ/ሮ ነጠሩ ወንድወሰን በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሥርዓተ ጾታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬከተር ባቀረቡት ጽሁፍ ስለ ሴቶች ጭቆና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሴቶች በተለያዩ የተዛቡ አመለካከቶችና የባህል ተፅእኖዎች ምክንያት በህበረተሰቡ ውስጥ የሚገባቸውን ቦታ ይዘው መብቶቻቸው ተጠብቀውላቸው በሀገር ልማት ውስጥ ሊያደርጉ የሚችሉትንና የሚገባቸውን ተሳትፎ እንዳያደርጉ የሚያስችሉ አሰራሮችና ድርጊቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም በአህጉር ደረጃ አፍሪካ የሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተነፈጉባት እንደነበር፣ ይህን ሁኔታ ለመቀየር የአፍሪካ ሴቶች አህጉሪቱን ከአውሮፓዊያን የቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ያበረከቱት እና የተጫወቱት ሚና ትልቅ እንደነበርና በአገራችንም በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ሥርዓቶች  የተፈራረቁባትና  ሥርዓቶቹም የየራሳቸው ባህሪ የነበራቸው ሲሆን፣በመሰረታዊ ይዞታቸው በህብረተሰቡ ጥያቄዎች አፈታትና በሴቶች ጥያቄዎች አፈታት ላይ ተቀራራቢነት እንደነበራቸው አሰረድተዋል፡፡

ወ/ሮ ወይዘር በላይ በቤተሰብ መምሪያ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ሴቶቸን እያጠቃ ስላለው የማህፀን ጫፍ ካንሰር ምንነት፣ አጋላጭ ሁኔታዎች፣ ምልክቶቹ፣  ምርመራ ሰለማድረግ፣ ግንዛቤ ስለመፍጠርና ስለህክምና መንገዱ በዝርዝር አሰረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ተምሳሌት ከሆኑ ሴቶች መካከል የሕግ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ የህይወት ልምዳቸውን ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ጥያቄዎችን በመጠየቅና አሰተያየት በመስጠት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በቆየው የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) ስብሰባ ላይ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርና ተጠሪ መ/ቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት