The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሥልጠና ተሰጠ


የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ከጥር 29-30 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሥልጠና ሰጠ፡፡
አቶ ትዕግስት ደበበ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሻሻል ላይ ያለውን የመንግሥት የግዥና የንብረት አሰተዳደር አዋጅ ዋና ዋና ገጽታዎችን በሚመለከት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣አዋጁን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያትም በአፈጻጸም የታዩ የአሠራር ጉድለቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤ መሆናቸውን፣ የአገሪቱን የልማት ግቦችን ለማሳካት በመንግሥት ግዥ የአገር ውስጥ ተወዳዳሪዎችን ተሳትፎ ማሳደግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ፣ በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ የተሟላ ለማድረግ አዳዲስ ድንጋጌዎችን ማካተት የግድ መሆኑ፣እንዲሁም የአዋጁን አወቃቀር በማስተካከል ለአፈጻጸም የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ መሆኑንና ስለማሻሻያው አዋጅ ዓላማና በአዋጁ ረቂቅ የተደነገጉ ዋና ዋና ለውጦችን  አስረድተዋል፡፡
አቶ ታደሰ ከበደ በመንግስት ግዥ አስተዳደር ከፍተኛ የግዥ ሥልጠና እና ሙያዊ ድጋፍ ባለሙያ ደግሞ በበኩላቸዉ በግዥ አፈጻጸም መመሪያ እና ደንቦች ይዘት እና የተፈጻሚነት ደረጃን በሚመለከት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ስለግዥ ዘዴዎች፣ስለመደበኛ የጨረታ ሰነዶች፣ስለአቅራቢዎችና የግዥ ባለሙያዎች፣ የግንባታ ዘርፍ ሥራ፣የምክር አገልግሎትና ስለኢትዮጵያ የግዥ የህግ ማዕቀፍና ሌሎች የአሰራር ዘዴዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡  
አቶ ነጋሽ ቦንኬ በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸምና ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የፌዴራል መንግስት ግዥ በሚመራባቸው የህግ ሰነዶችን በሚመለከት ሥልጠና የሰጡ ሲሆን፣ሰለፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001፣ለዚሁ አዋጅ አፈጻጸም ዓላማ የወጣውን የግዥ አፈጻጸም መመሪያ እና የመንግስት የግዥ አፈጻጸም ማንዋል፣ ተሻሽለው ስለወጡ መደበኛ የጨረታ ሰነዶች፤ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም ሂደት አቅራቢዎች ያላቸው መብትና ግዴታዎች ምን ምን እንደሆኑ፣ በግዥና ንብረት አሰተዳደር አዋጅና በግዥ አፈጻጸም መመሪያው ለጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ስለተሰጡ መብቶች፣ በአቅራቢዎች በኩል ሰለሚታዩ ግድፈቶች፣ በፌዴራል መንግስት ግዥ ላይ አቅራቢዎች በመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች ላይ የሚያቀርቡት አቤቱታ እና የመንግስት መ/ቤቶች በአቅራቢዎች ላይ የሚያቀርቡት የጥፋተኝነት ሪፖርት ዙሪያ በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
አቶ ሙሉ አድገህ በፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የአገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ ባለሙያ ሰለሰነዱ ዓላማ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ለማበረታታት የወጣውን የመንግስት ግዥ መመሪያን መሠረት በማድረግ በልዩ አስተያየት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በተሰራው ስራ ኢንተርፕራይዞች ያጋጠማቸውን ችግር የመለየትና የመፍትሄ ሃሳብ በማሰቀመጥ፣የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ መሆኑንና ጥቃቅንና  አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በጨረታ ሂደት ያጋጠሙ  ችግሮችና  መፍትሄዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የመንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በግዥ አፈጻጸም ዙሪያ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ጋር በተካሄደዉ ሥልጠና ላይ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች አሰተያየቶችም የተነሱ ሲሆን፤ ለተነሱ ጥያቄዎችና አሰተያየቶች መልስ ተሰጥaል፡፡
ከመ.ግ.ን.አ.ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት