The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

29ኛው የዓለም ኤች አይቪ ኤድስ እና 26ኛው የጸረ-ፆታ ጥቃት ቀን ተከበረ

የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን እና ከመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን የዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን እና የጸረ—ጾታ ጥቃት ቀን ህዳር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አዳራሽ በድምቀት አከበረ፡፡

አቶ ይገዙ ዳባ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በመክፈቻው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት በዚህ ዓመት የዓለም ኤድስ ቀን በዓለም አቀፍ እና በአገራችንም “አሁንም ትኩረት ለኤች. አይ.ቪ መከላከል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ እንደሚገኝና የዚህ በዓል ዓላማም በሽታው እያደረሰ ያለውን ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ጉዳት ለመከላከል፣ ብሎም ለማስቆም እንዲሁም በበሽታው የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና ለመንከባከብ አድሎ እና መገለልን በማስወገድ አገራችንን ጨምሮ የዓለም መንግሥታትና መላው የዓለም ሕብረተሰብ ስለበሽታው ትኩረት ሰጥቶ እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም ዋና ዳይሬክተሩ በዘንድሮው ዓመት የዓለም ኤድስ ቀንና የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን በጋራ ሲከበር ጾታዊ ጥቃትን በመከላከል የኤች.አይ.ቪ ስርጭት መጠንን ለመቀነስ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ከግምት በማስገባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ ከዋኒ ይብራ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን የጤናና ሥነ—ምግብ ፕላን ከፍተኛ ባለሙያ በዓለም ለ29ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ28ኛ ጊዜ የሚከበረውን የኤድስ ቀን በማስመልከት የግንዛቤ ማስጨበጫ የሰጡ ሲሆን፣ በየዓመቱ ቀኑ ሰለሚከበርበት ምክንያት፡- ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር፤ በኤች. አይ.ቪ እና ኤድስ የተጎዱትን ወገኖች ለመርዳትና ለማበረታታት፤ ጥናቶችን ለህብረተሰቡ ለማቅረብና መረጃን ለመስጠት፤ የባለቤትነትን ስሜት ለመፍጠር መሆኑንና በአገር ደረጃም የ2008 ዓ.ም. ኤች.አይ.ቪ. ኤድስ ህክምና አገልግሎት አፈጻጸም ከዕቅድ አንጻር ምን ይመስል እንደነበር፣ አሁንም ያሉት ተግዳሮቶችና ስጋቶች ምን እንደሆኑ እና የባለድርሻ አካላት /የመንግስት ሴክተሮች/ ሚና ጎልቶ መውጣት እንዳለበትና ይህም ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ወ/ሮ ትብለፅ ቡሽራ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ  የሆኑት በዓለም ለ26ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ11ኛ ጊዜ የሚከበረውን የጸረ—ጾታ ጥቃት ቀንን በሚመለከት ጾታዊ ጥቃትና አካላዊ ሥነ-ልቦና ምንድነው? ጾታን መሰረት አድርገው በህብረተሰቡ፣ በቤት ውስጥ እና በስራ አካባቢ ስለሚያጋጥሙ ጥቃቶች፣ ስለ ህግ ማዕቀፍ ጾታዊ ጥቃትን በሚመለከት ከህገ መንግስቱ አንጻር እየቃኙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰጥተዋል፡፡

ለግማሽ ቀን የቆየው የዓለም የኤድስ ቀን እና የዓለም አቀፍ የጸረ—ጾታ ጥቃት ቀን በስነ-ፅሁፍና ኤች.አይቪን በሚመለከት በቃል ምስክርነት በመታጀብ የደመቀ ሲሆን የሶስቱም መ/ቤት ሃላፊዎችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት