The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን በሚመለከት በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚተገበርበት ማስፈጸሚያ ዕቅድ ላይ ስልጠና ተሰጠ

የፌደራል መንግስት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ከመንግስት የግዥና የንብረት ማሰወገድ አገልግሎት ጋር በጋራ በመሆን በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚተገበርበት ማስፈጸሚያ ዕቅድን በሚመለከት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አሰተባባሪነት ለኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከጥር 9—12/2009 ዓ.ም. በመንግስት የግዥና የንብረት ማሰወገድ አገልግሎት አዳራሽ ስልጠና ተሰጠ፡፡

ዶ/ር አብርሃም ተከስተ  የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ሥልጠናውን የሰጡ ሲሆን፣ ዓላማውም የፐብሊክ ሰርቪሱ የልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥቱን ባህርያትና የሚጠበቅባቸውን ገንቢ ሚና በውል ተገንዝቦ ለላቀ የህዝብ አገልጋይነት  እንዲነሳሳ ማድረግ፣ በአገልግሎት የሚስተዋሉ በአስተሳሰብና በተግባር የህዝብ አገልጋይነትና ውጤታማነት የሚጎዱ ዝንባሌዎችን በዲሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል በማስተካከል የቀሪ GTP II ዓመታት ተግባራትን በላቀ ደረጃ እንዲፈጽሙ የሚያስችል ዝግጁነትና ተነሳሽነት መፍጠርና በአገራዊ የለውጡ ሂደት ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ አቅጣጫ ላይ ግልጽነት እንዲዳብር በማድረግ በአመራሩና በሠራተኛው መሀከል ጠንካራ መተማመንና መደጋገፍን መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመቀጠልም ሚኒስተሩ በዓለማችን የሚታዩ መንግሥታትን በአጠቃላይ በ3 በመመደብ እንደሚቻል ገልጸው ስለ ሊበራል ካፒታሊሰታዊ መንግስት፣ ስለ ዕዝ አኮኖሚ ሥርዓት መንግስትና ስለ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት ምንነትና መገለጫዎች ያስረዱ ሲሆን፤ ከነዚህም ለምን ልማታዊ መንግሰት እንደተመረጠም ሲያብራሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እድገት ጎዳና የሚያደርሰ እንደሆነና ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ ህዝባዊ ወገናዊነት ያለውና ልማት የህዝቡ ጉዳይ ነው ብሎ የሚያምን መንግሥት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሥልጠናውም የቡድን ወይይት ክፈለ ጊዜ የነበረ  ሲሆን፣ በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ለ3 ቀናት በቆየው በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄን በፐብሊክ ሰርቪሱ የሚተገበርበት ማስፈጸሚያ ዕቅድን በሚመለከት ስልጠና ላይ የአጄንሲው የበላይ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡

 

የፌ.መ.ግ.ን.አ.ኤ ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት