The FDRE Public Procurement and Property Authority

በኢፌዲሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን

የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጠ

የፌዴራል መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ በመንግስት ግዥ አፈጻጸም፣በንብረት አስተዳደር፣በተሽከርካሪ አያያዝ እና በነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከፍትህ አካላት እና ከሚዲያ ተቋማት ለተውጣጡ የተቆጣጣሪነት ሚና ላላቸው ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከግንቦት 22—26/2008ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ሰጠ፡፡
የሥልጠናው ዓላማም በዋናነት ግዥ ከፍተኛዉን የመንግሥት በጀት ስለሚይዝ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገውና የተሻለ የግዥ ስርዓት ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለዉ መሆኑንና ግልጽ፣ ዘመናዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የመንግስት ግዥና  ንብረት አስተዳደር ማስፈን እንደሆነ ተገልጿል፡፡
አቶ ነጋሽ ቦንኬ በመንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የግዥ አፈጻጸም ንብረት ማስወገድ አቤቱታ ማጣራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣አቶ ታደሰ ከበደ በመንግስት ግዥ አሰተዳደር ዳይሬክቶሬት የግዥ ስልጠናና ሙያዊ ድጋፍ ባለሙያ፣አቶ ወርቁ በዛብህ በመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ባለቤት የሌላቸው የመንግስት ንብረቶች ከፍተኛ ባለሙያ ስልጠናውን የሰጡ ሲሆን ስለመንግስት ግዥ አጠቃላይ ገጽታ፤ ስለመንግስት ግዥ ዓላማና መርሆዎች፣ ስለ  ግዥ ዕቅድ፣ስለተፈቀዱ የግዥ ዘዴዎች፣ስለመደበኛ የጨረታ ሠነዶች፣ስለጨረታ አከፋፈትና ግምገማ፣ ስለምክር አገልግሎት ግዥ፣ ስለውል አሰተዳደር፣ ስለ ዋጋ ማስተካከያ፣ ስለ ዋና ዋና ተግባርና ኃላፊነቶች፣ ከግዥ ባለሙያዎችና ከአቀራቢዎች  የሚጠበቅ ሥነ ምግባር እንዲሁም ስለመንግስት ንብረት አያያዝ፣ትርጓሜ እና ዓላማ ስለመንግስት ንብረት አስተዳደር ተግባራት፣ ስለሰቶክ አስተዳደር፣ስለ ቋሚ ንብረት አስተዳደር፣ ስለ መንግሥት የግዥና የንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ሚና፣ስለ አጠቃላይ ቆጠራ እንቅስቃሴና የመዝገብ ዝግጅት ሂደት፣ ለቋሚ ንብረቶች ዋጋ ስለመመደብ እና ስለ ቋሚ ንብረቶች የእርጅና ቅናሽ በዝርዝር ገለጻ አድርገዋል፡፡
በቀረበው ገለጻና ማብራሪያ በተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ለጥያቄዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ሰልጣኞች በቆይታቸዉ ስልጠናው ጥሩ አቅም እንደፈጠረላቸውና የነበረባቸውን ክፍተት ለመሙላትና ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት በየመ/ቤታቸው ሲመለሱ  ወደ ተግባር ለመለወጥ አጋዥ እንደሚሆንላቸው ገልጸዋል፡፡
ለአምስት ቀናት በቆየው በመንግስት ግዥ አፈጻጸም፣በንብረት አስተዳደር፣በተሽከርካሪ አያያዝ እና በነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ከፍትህ አካላት እና ከሚዲያ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡