የሀገራችንን ልማት ለማፋጠን እና ለዜጎቻችን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነትና በትብብር መስራት ይኖርብናል። ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ

(መጋቢት 16/2018 ዓ.ም)፣ የኢፌዴሪ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽ፣ ቀልጣፋ እና ተደራሽ ለማድረግ ከክልል የግዥና ንብረት እንዲሁም ከፋይናንስ ሀላፊዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር እያካሄደ ይገኛል። በምክክር መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት መስቀሌ እንደገለጹት የመንግስታዊ አገልግሎት ዋና መሠረቶች የግልጽነት፣ የተጠያቂነት፣ የቅልጥፍና እና የተገቢ የገንዘብ አጠቃቀም ሲሆኑ ይህንን ለማሳካት ደግሞ ዲጂታል ስርዓቶችን መጠቀም አስፈላጊ እንደተገኘ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት (e-GP sytem) የግዥ ሂደቶችን በማቀላጠፍ፣ የሰው ጣልቃ ገብነትን በመቀነስ እና የመረጃ ግልጽነትን በማሳደግ የሀገር ሀብት እንዲጠበቅ ይረዳል ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሽከርካሪ ስምሪትና አስተዳደርና ነዳጅ አጠቃቀም ስርዓትን (e-fleet management system) እና ሌሎችንም የአሰራር ስር ዓቶች ዘርግቶ በውጤታማነት እየሰራባቸው ይገኛል ሲሉ አመላክተዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በንግግራቸው የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓት ስኬት በክልልና በከተማ አስተዳደሮች ያለው አገልግሎት እና ተሳትፎ ላይ የሚመሰረት በመሆኑ ተቋማትን በአቅም ማጎልበት፣ ባለሙያዎችን ማብቃት፣ ቴክኖሎጂን ማስፋፋት እና የህግ አፈጻጸምን ማጠናከር የሁላችንም ትኩረት መሆኑ ይኖርበታል ብለዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ አፈጻጸምን በገለጹበት ንግግራቸው ወደ ክልሎች እየወረደ እንደሆነና በተለይም በአዲ አበባ ከተማ መስተዳደር ከፓይለት 13 ተቋማት በተጨማሪ 55 ተቋማት ስር ዓቱን እየተገበሩ መሆናቸው፣ በኦሮሚያ ክልል በ16 ተቋማት መተግበር መቻሉ፣ ሌሎች 7 ክልሎች ስር ዓቱን ለመተግበር በመሰረተ ልማትና በቴክኖሎጂ ዝግጁ መሆናቸው እንዲሁም ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ሶማሌ፣ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለመጀመር የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደተሰጣችውና ሌሎችንም ክልሎች ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህግ ማዕቀፎችን ከመተግበር አንጻርም የግዥና ንብረት አዋጅ 1333/2016 ስራ ላይ ከመዋሉ ጋር ተያይዞ ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮችም ከፌደራሉ ጋር የተጣጣመ የአዋጅ እና መመሪያ ዝግጅት እንዳደረጉና አብዛኛዎቹ እንዳጸደቁ ገለጸዋል።
ክብርት ወ/ሮ መሰረት በማጠቃለያ ንግግራቸው ሁላችንም የሀገራችንን ልማት ለማፋጠን እና ለዜጎቻችን የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት፣ በትብብር እና በአመራር ኃይል መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡት በመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን የግዥና ንብረት ማሻሻያና አቅም ግንባታ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ተጓዴ በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን በውጤታማነት ለመምራት የህግ ማዕቀፎችን ከማሻሻል ጀምሮ ሰፋፊ ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝና ክልሎችም የህግ ማዕቀፎቻቸውን ከፌዴራሉ የግዥና ንብረት የህግ ማዕቀፎች ጋር ተቀራራቢ እንዲሆን ለማድረግ ተከታታይ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ እና አብዛኞቹ ክልሎችም የህግ ማዕቀፎቻቸውን ከፌዴራሉ የግዥና ንብረት ህጎች ጋር የማጣጣም ስራ እንደሰሩ አመላክተዋል።
በሌላ በኩል የመንግስት ኤሌክትሮኒክ ግዥ ስርዓትን (e- GP System) ወደ ክልሎች ማወረድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ገለጻ ያደረጉት የፒራጎ መስራችና ማናጀር አቶ እውነቱ አበራ እንደገለጹት ስርዓቱን ወደ ክልሎች ለማውረድ የመንግስት ግዥና ንብረትም ይሁን ፒራጉ ዝግጁ እንደሆኑ ይልቁንም ክልሎች አስቀድመው ስምምነት መፈራረም፣ ፕሮጀክቱን የሚመራና ሀላፊነት የሚወስድ ባለሙያ መመድብ፣ የስልጠና ማዕከላትን ማሟላትና መሰል ጉዳዮችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው አብራርተዋል።
በመጨረሻም ከተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው የእለቱ የምክክር መድረክ ተጠናቋል።





0 Comments